የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሚድ ዋይፈሪዎች ማህበር ለኮሮና መከላከል የ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የህክምና ቁሳቁስ ደገፈ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሚድ ዋይፈሪዎች ማህበር ለኮሮና መከላከል የ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር የህክምና ቁሳቁስ ደገፈ
አዳማ /ኢዜአ/ ነሐሴ 23/2012 የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሚድ ዋይፈሪዎች ማህበር በኮሮና ምክንያት የእናቶችና ህፃናት መደበኛ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ እንዳይስተጓገል ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን የህክምና መርጃ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
ማህበሩት ለአዳማ ሪፌራል ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ የአፍና አፍንጫ መሸፈሻ ጭምብል፣ የእጅ ጓንት፣ የልብና ደም ግፊት ማዳመጫ መሳሪያዎችን ነው ለሆስፒታሉ ለሁለተኛ ጊዜ ድጋፍ ያደረገው።
የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ የሺጥላ ተስፋዬ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት በኮሮና በሽታ ምክንያት የእናቶችና ህፃናት ጤና እንዳይስተጓገል ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸውን የህክምና መርጃ ቁሳቁስ ለጤና ጣቢያዎችና የደንበኞች ጫና ላለባቸው ሆስፒታሎች ድጋፍ አድርገናል ብለዋል።
በተለይ በአሁኑ ወቅት ለወላዶችም ሆነ ለአገልግሎት ሰጪ የህክምና ባለሙያዎች የኢንፌክሽንና ኮሮና በሽታ መከላከያ መሳሪያዎች እንዲሁም የስራ ጋዎን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ማህበራቸው የመደበኛ ጤና አገልግሎት አሰጣጥን ለማገዝ እስከ አሁን የተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶችና ባለሃብቶችን በማስተባበርና ሀብት በማሰባሰብ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
በሆስፒታሉ ድጋፉን የተረከቡት የመዋለጃ ክፍል ሃላፊ አቶ ተስፋዬ ቱፋ በበኩላቸው ማህበሩ የእናቶችና ህፃናት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ለመደገፍ የሚረዱ መሳሪያዎችን ለሁለተኛ ጊዜ ድጋፍ መስጠቱን ጠቅሰው ሌሎች የሙያ ማህበራትም ይህን ፈለግ በመከተል ሊያግዙን ይገባል ብለዋል።
ሆስፒታሉ በወር ከ750 በላይ ለሚሆኑ እናቶች የወሊድ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ያሉት አቶ ተስፋዬ የእንፌክሽንና የኮሮና በሽታ መከላከያዎቹና መሳሪያዎቹ እጅጉን ያስፈልጉናል ብለዋል።
በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሴቶችና ህፃናት ዳይሬክተርና የማህበሩ የቦርድ አባልሲስተር አስቴር ተሾመ እንደገለጹት በኮሮና ምክንያት በጤና ባለሙያዎች ላይ በህክምና መርጃ ቁሳቁስ እጥረት ልፈጠር የሚችለውን ጫና ለመቀነስ ማህበሩ ከሚኒስቴሩና ከክልል የጤና ቢሮዎች ጋር እየሰራ አንደሚገኝ ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፣ የጤና ቢሮዎች፣ ባለሃብቶችና ለጋሽ ተቋማት ባደረጉት ርብርብ እስከ አሁን በአቅርቦት እጥረት የተስተጓጎለ የእናቶችና ህፃናት ጤና አገልግሎት የለም ብለዋል።
አሁን እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሀብት የማሰበሳብ ስራ እየሰራን ነው ያሉት ሲስተር አስቴር፤ ባለሃብቶቹ በያሉበት ከተሞችና ዞኖች በሽታውን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በማገዝ ረገድ አጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።