ለህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ የድርሻችንን እንወጣለን- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ የድርሻችንን እንወጣለን- የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች
አርባ ምንጭ ነሐሴ 24/2012 (ኢዜአ) ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ቀሪ ስራ መጠናቀቅ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በተካሔደው 39ኛው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ህብረት ጉባዔ ላይ ተሳታፊዎች አስታወቁ።
በተጠናቀቀው ጉባኤ ላይ ከነበሩ ተሳታፊዎች መካከል የዲላ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ ሐና ነገሰ ለኢዜአ እንደገለጸችው ግድቡ የሁሉም ኢትዮጵያዊ አሻራ ያረፈበት አንጡራ ሀብት ነው።
በተለይ የመጀመሪያው ዙር የግድቡ ውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ በመከናወኑ ወደር የሌለው ደስታ እንደተሰማት ገልፃ ለቀሪው ስራ መጠናቀቅ ቦንድ በመግዛት የበኩሏን ድጋፍ በማድረግ ተሳትፎዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታውቃለች።
“አብዛኛው የሀገሪቱ ዜጎች በኤሌክትሪክ እጥረት ጨለማ ውስጥ ለመኖር ተገደዋል” የምትለው ሀና “ይህ ታሪክ የሚቀይር ተግባር እየተገባደደ ስለሆነ ኩራት ተሰምቶኛል” ብላለች።
ሌላው የመድረኩ ተሳታፊና የአርሲ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ ኢያሱ ጌቱ በበኩሉ የህዳሴው ግድብ ከአገራችን ህልውና ጋር የሚያያዝ ታላቅ ፕሮጀክት በመሆኑ የሁሉንም ድጋፍና ተሳትፎ ይሻል።
“መንግስት የታችኞች የተፋሰስ አገራትና የሃያላንን ጫና በመቋቋም የግድቡን ውሃ ሙሌት በማከናወኑ ትልቅ ወኔ ተሰምቶኛል” ይላል።
“ምንም እንኳን ተማሪዎች ብንሆንም ግድቡ ለአገራችን ብልጽግና ወሳኝ በመሆኑ በግሌ ቦንድ ከመግዛትም በላይ ተማሪዎችን በማስተባበር የበኩሌን እወጣለሁ” ብሏል።
ለግድቡ ቀሪ ስራ መጠናቀቅ መደበኛው ትምህርት በሚጀመርበት ወቅት ቦንድ ለመግዛት በተማሪ ህብረት በኩል ዕቅድ መያዙን የገለጸው ደግሞ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ህብረት ምክትል ፕሬዝዳንትና የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ አብርሃ አረፋይኔ ነው።
“እኛው እንደ ጀመርነው እኛው እንጨርሰዋለን” የሚለው ወጣቱ “እኛ ተማሪዎች በግድቡ ብቻ ሳይሆን በአገራችን ገጽታ ግንባታ ላይም አዎንታዊ አሻራ ማኖር ይጠበቅብናል” ብሏል።