ቀጥታ፡

ኩባንያው ቡናን በቴክኖሎጂ አስደግፎ እያለማ ነው

 አዲስ አበባ ነሐሴ 23/2012 (ኢዜአ) ቀርጫንሼ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ቡናን በቴክኖሎጂ አስደግፎ በማልማት ውጤታማ መሆኑን አስታወቀ፡፡ ኩባንያው ከብራዚል ባገኘው ተሞክሮ ቡና በመስኖ እያለማ ነው፡፡ 

 የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣንና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ኩባንያው በምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ በቴክኖሎጂ ተደግፎ የሚለማውን ቡና ጎብኝቷል፡፡

ኢትዮጵያ በቡና ምርት ከዓለም ሰባተኛን ደረጃ ስትይዝ፣ ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ መሆኗ ይታወቃል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ለውጭ ገበያ የምታቀርበው ቡና በባህላዊ መንገድ ይለማል፡፡  በዚህም ቡናን በዛፍ ጥላ ስር ብቻ ያመርታሉ፡፡

ቀርጫንሼ የተባለው ኩባንያ በምዕራብ ጉጂ ዞን አባያ ወረዳ ከብራዚል ባገኘው ቴክኖሎጂ መሠረት ቡናን በመስኖ ስርዓት እያለማ ይገኛል፡፡

የኩባንያው ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ባለቤት አቶ እስራኤል ደገፍ ለኢዜአ እንዳሉት ቡናን በመስኖ የማልማት ቴክኖሎጂ ለአገሪቱ አዲስና የመጀመሪያው ነው ብለዋል፡፡

ተሞክሮውም ከደቡብ አሜሪካ አሀጉር ብራዚል የተገኘ ነው ይላሉ፡፡

ድርጅታቸውም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና አገሪቷ ከቡና የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት እየሰሩ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡

ቴክኖሎጂው አሁን በሄክታር የሚመረተውን ከአምስት ኩንታል ያልበለጠ ቡና ወደ ከአራት እስከ አምስት እጥፍ ያሳድገዋል ብለዋል፡፡  

ቴክኖሎጂውም የቡናውን ምርት ከማሳደግ በላይ፤ የውጭ ምንዛሪን ግኝትን በዚያው ልክ እንደሚያሳድግ አቶ እስራኤል አስታውቀዋል፡፡

በቀርጫንሼ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የእርሻዎች አስተባባሪ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደጀኔ ዳባ እንዳሉት ቴክኖሎጂው ከሰው ንክኪ ነጻ ሆኖ በራሱ የሚሰራ ነው ፡፡

የከርስ ምድር ውሃን በማውጣት የሚሰራው ይህ ቴክኖሎጂ ውሃው ወደ ማጠራቀሚያው ከተወሰደ በኋላ በጥልቅ መስኖ /Deep irrigation/ ለእያንዳንዱ ተክል በተዘረጋው ገመድ በኤሌክትሪክ አማካኝነት ይደርሳቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኩባንያው ዋና ዓላማ ቴክኖሎጂውን ተጠቅሞ በማምረት ለራሱ ከመጠቀም ባለፈ ለሌሎች ልምዱን እያካፈለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ሕዝብ ግንኙኘትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሣህለ ማርያም ገብረ መድህን  ባለስልጣኑ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተለይ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ለሚጠቀሙና ለሚያሰፉ አካላት ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል፡፡

ቴክኖሎጂው የአገሪቱን ቡና ምርትና ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን መጠን እንዲጨምር ያደርጋል ብለዋል፡፡

ይህም የአገሪቷን የውጪ ምንዛሪ ግኝት እንደሚያሳድገው ጠቁመዋል፡፡

ኩባንያው በቴክኖሎጂ  የሚያለማው  ቡና  በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም