ቀጥታ፡

ኮሮና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ጫና እንዳያሳድር አሰሪዎች የሰራተኞችን ጤንነት መጠበቅ አለባቸው -ሚኒስቴሩ

ደብረ ብርሃን፣ ነሐሴ 22/ 2012 (ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ሊያሳድር የሚችለውን ጫና ለመቀነስ የበሽታውን መከላከያ መንገዶች በመተግበር አሰሪዎች የሠራተኞችን ጤንነት መጠበቅ እንዳለባቸው የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ።

ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስ ወረርኝ ለመከላከል እንዲያግዝ በደብረብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርክ ያዘጋጀውና "እኔ ኃላፊነት አለብኝ እናተስ" የሚል የማስገንዘቢያ ቢል ቦርድ ዛሬ አስመርቋል።

በዚህ ወቅት የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ አየለች እሸቴ እንደገለጹት መንግሥት በአሠሪና ሠራተኞች መካከል የኢንዱስትሪ ሰላም እንዲሰፍን የሥራ ላይ ፕሮቶኮል አውጥቶ ሥራ ላይ አውሏል።

አሠሪና ሠራተኞች በመተሳሰብና መደጋገፍ ላይ ተመሥርተው እንዲሰሩም የወጣው ፕሮቶኮል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል።

አሠሪዎች ምርታማነታቸው የሚያድገው የሠራተኞቻቸውን ጤንነት ሲጠብቁ መሆኑን ተገንዝበው ኮሮናን የመከላከያ መንገዶችን ማስተግበርና ለዚህም የሚያገለግሉ ቁሶችን ማቅረብ እንዳለባቸው አሳሰበዋል።

ኢንዱስትሪዎች ወረርሽኙን በመከላከል ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የጀመሩትን የተጠናከረ ተግባር ለመደገፍ፣  ሠራተኞች የራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ጤንነት እንዲጠብቁ ለማገዝ  የዕለት ከዕለት የማስገንዘቢያ ቢል ቦርድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሣሁን ፎሎ በበኩላቸው አሰሪ ይሁን ሠራተኞች ሥራቸው ቀጣይነት የሚኖረው ወረርሽኙን በጋራ መከላከል ሲችሉ ብቻ መሆኑን ተገንዝበው ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የተዘጋጀው ቢል ቦርድ ሠራተኞች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከበሽታው በመጠበቅ ለምርታማነት ተግተው እንዲሰሩ ያግዛል ብለዋል።

ሥራ ከተበደለ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚደርሰው ጫና ከፍ ያለ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትና የኢንዱስትሪ አሠሪዎች ኮንፌደሬሽን ዋና ፀሐፊ አቶ ዳዊት ሞገስ ናቸው።

ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ሥራ እንደቀድሞው ሊቀጥል የማይችል በመሆኑ በሽታውን መከላከልና ሥራውን አቀናጅቶ በማስኬድ የኢንዱስትሪውን ሰላም እንደሚጠብቅ ተናግረዋል።

ቢል ቦርዱ የበሽታው ሥርጭት በመከላከሉ ረገድ የሠራተኛውን የዕለት ተዕለት ግንዛቤ ለማሳደግ እንደሚያገዝ የደብረ ብርሃን ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ መርከብ ለማ ገልጸዋል።

በቢል ቦርድ ምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ከፌደራል፣ ዞን እና ከተማ አስተዳደር የተውጣጡ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም