ቀጥታ፡

በግድቡ ግንባታ ሥራ እየተሳተፉ ያሉ ሠራተኞችን ለማመስገን ያለመ የሙዚቃ ኮንሰርት ሊዘጋጅ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23/2012 (ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በሚገነባበት ቦታ ላይ በግድቡ ግንባታ ሥራ እየተሳተፉ ያሉ ሠራተኞችን ለማመስገን ያለመ የሙዚቃ ኮንሰርት ለማቅረብ መታሰቡ ተገለጸ።

ኮንሰርቱ የአካባቢውን ከፍተኛ ሙቀትና ሐሩር ተቋቁመው በግድቡ ግንባታ ሥራ ላይ እየተሳተፉ ያሉ ሠራተኞችን ለማመስገን ያለመ መሆኑም ተገልጿል።

የቴአትር ጥበባት ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ጋሻው ሽባባው ለኢዜአ እንዳሉት የጥበብ ሰዎች የሕዳሴው ግድብ ግንባታ የመሠረተ ድንጋይ ከመጣሉ አስቀድሞ ቁጭታቸውን በዘፈንና በሌሎች የኪነጥበብ ውጤቶች ሲገልጹ ኖረዋል።

ግድቡ ከተጀመረ በኋላም የኪነጥበብ ባለሙያዎቹ በርካታ ሥራዎችን ማበርከታቸውን አስታውሰው፣ በቀጣይም ይህ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ትላልቅ መድረኮችን በማዘጋጀት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ስለግድቡ በተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ለማድረግ እንደሚሰራም አቶ ጋሻው ተናግረዋል።

"የሕዳሴው ግድብ እየተገነባ ባለበት ሥፍራ ያለውን ሐሩሩና የእሳት ንዳድ ተቋቁመው እየሰሩ ያሉትን ሠራተኞች ማመስገን ያስፈልጋል" ያሉት አቶ ጋሻው፣ ለእዚህም የሙዚቃ ኮንሰርቱን ለማቅረብ ፕሮግራም መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

በተጨማሪም "የዓባይ ወንዝ ልጆች" በሚል በአርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ ፕሮጀክት መቀረጹንና የ11ዱ የዓባይ ተፋሰስ አገራት አርቲስቶችን እንደሚያካትት አመልክተዋል።

የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰርፀ ፍሬስብሐት በበኩላቸው "ኪነጥበቡ ለበርካታ ዓመታት በዓባይ ጉዳይ ተክዟል" ብለዋል።

የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ አንስቶ የኪነጥበብ ባለሙያዎች ለግድቡ በርካታ ድጋፎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅትም የጥበብ ሰዎች በሕዳሴው ግድብ ላይ ኮንሰርት ለማቅረብ ዕቅድ እንዳላቸው ለቢሮው መሳወቃቸውን ተናግረዋል።

"በኮንሰርቱም የኪነጥበብ ባለሙያዎች አገራዊ ጥበብን የወከለ ሥራ በማቅረብ በሕዳሴው የግንባታ ሥራ ላይ እየተሳተፉ ያሉትን ያመሰግናሉ" ብለዋል።

በተመሣሣይ በብሔራዊ ቴአትር የታሪክ፣ የፍልስፍናና የሥነሰብዕ ተመራማሪዎችና ሊቃውንት ስለግድቡ ንግግር እንደሚያደርጉ አቶ ሰርፀ ጠቁመዋል።

በመገናኛ ብዙሃን ትኩረት የሚሰጠውን የሙዚቃ ኮንሰርት ለማሰናዳት ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑንም ገልጸዋል።

ኮንሰርቱ የሚቀርብበት ጊዜ ወደፊት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ የሚወሰን መሆኑም ተገልጿል።

በኪነጥበብ ባለሙያዎቹ ለሕዳሴው ግድብ የሚደረገው ድጋፍ ዓመቱን ሙሉ በተለያዩ ዝግጅቶች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተመልክቷል።

"የጥበብ ባለሙያዎች የሚሰሩት ሥራ የአዳራሽ ሆኖ እንዳይቀርና ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን የመገናኛ ብዙሃን ሚና የጎላ ነው" ያለችው ደግሞ አርቲስት ሕይወት አራጌ ናት።

መገናኛ ብዙሃን በግድቡ ዙሪያ እየሰሩ ያሉትን ሥራ አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸውም ተናግራለች።

የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ከተጀመረ ጀምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የበኩሉን ሲያደርግ እንደነበር ያስታወሰችው አርቲስቷ፣ በቀጣይም ሁሉም በየዘርፉ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቃለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም