በመዲናዋ በተያዘው በጀት ዓመት ለሕዳሴ ግድብ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ በተያዘው በጀት ዓመት ለሕዳሴ ግድብ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 23/2012(ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ በተያዘው የ2013 በጀት ዓመት ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከ180 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የከተማዋ የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት አስታወቀ።
በከተማዋ እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ከ789 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱም ተነግሯል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ተሳትፎ ምክርቤት አባላት ጉባኤ ዛሬ ተካሂዷል።
በጉባኤው ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር ዓባይን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ቢሮ ኃላፊዎች፣ በከተማዋ የሚገኙ የኪነጥበበ ባለሙያዎችና የሃይማኖት አባቶች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት የከተማዋ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ እንዳሉት፣ በ2012 በጀት ዓመት በከተማዋ ለግድቡ ግንባታ 100 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል።
በዘንድሮ ዓመት በሚከናወኑ የህዝብ የንቅናቄ ሥራዎችና ተጨማሪ ተግባራት ከ789 ሚሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ የግድቡ የመጀመሪያ ደረጃ ውሃ ሙሌት መበሰሩና ከግንቦት ወር 2012 ዓ.ም ጀምሮ የሕዳሴው ግድብ ዋንጫ በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለከተሞች እየተዘዋወረ መሆኑ ለሀብት አሰባሰብ ሥራው መልካም ዕድል መፍጠራቸውን አስረድተዋል።
በዚህም በተጀመረው በጀት ዓመት እስካሁን ባለው ሂደት ብቻ ከ182 ሚሊዮን 350 ሺህ ብር በላይ መሰብሰቡን አስታውቀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር ዓባይ በበኩላቸው ግድቡ በአሁኑ ወቅት ተስፋ በሚጣልበት ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።
"ግድቡ የኢትዮጵያን በነፃነት የመልማት መብት ማሳያ በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሕዳሴው ግድብ ላይ የጋራ መግባባትና አንድነቱ እንዲያጠናከር መስራትና በቂ መረጃ መስጠት ያስፈልጋል" ብለዋል።
ከኮሙዩኒኬሽንና ዲፕሎማሲ አኳያ ብሔራዊ ምክር ቤቱ የሚያከናውናቸው ተግባራት እንዳሉ ሆነው የከተማዋ አስተዳደርም ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
ለግድቡ ድጋፍ በማሰባሰብ በኩል ተደራሽ ያልሆኑትን በመለየት መስራትና ዋንጫውም በወጣለት መርሃግብር መሰረት በየክፍለከተማው እየዞረ ገቢው እንዲጠናከር የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አስገንዝበዋል።
የምክርቤቱ አባላት ለሕዳሴው ግድብ ሀብት ለማሰባሰብ የሚደረገውን የንቅናቄ ሥራ ለማገዘ ተግተው ሊሰሩ እንደሚገባም ነው የገለጹት።
"የሕዳሴው ግድብ በዘላቂነት ኃይል እንዲያመነጭ አስተዋፅኦ ለሚኖረው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ሁሉም ሊረባረብ ይገባል" ያሉት አቶ ዣንጥራር፣ ከተማ አስተዳደሩ አካባቢን በማልማትና ለግድቡ ገንዘብ በማዋጣት በኩል የድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የምክርቤቱ አባላትም ሀብት በማሰባሰብም ሆነ ተገቢውን መረጃ በመስጠት በኩል የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የኮተቤ ሜትሮፖሊቲያን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ብርሃነመስቀል ጠና እንዳሉት፣ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ለግድቡ ግንባታ ለ4ኛ ጊዜ የቦንድ ግዢ ፈፅመዋል።
በቀጣይም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመው፣ የሕዳሴው ግድብ የአንድ ሰሞን ሳይሆን የሁልጊዜ አጀንዳ እንዲሆን ሁሉም ሚናውን እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አርቲስት ደሳለኝ ኃይሉ በበኩሉ፣ የሕዳሴው ግድብ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሶ፣ የግድቡ ግንባታ ሥራ እስኪጠናቀቅ ድረስ በሙያው የተቻለውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አረጋግጧል።
ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው በተያዘው ዓመት በከተማ አስተዳሩ ለመሰብሰብ የታሰበው ገንዘብ እንዲሰበሰብ እና አፍራሽ ፕሮፓጋንዳዎችን ለመመከት ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።