ቀጥታ፡

ገበታ ለሀገር የልማት ፕሮጀክት ሁሉም ዜጋ ቀና ምላሽ ይጠበቅበታል.. የፕላን ኮሚሽን

ሐዋሳ፣ ነሐሴ 23/2012 (ኢዜአ) ገበታ ለሀገር የልማት ፕሮጀክት ስኬታማነት ሁሉም ዜጋ ድጋፍ ለማደረግ ቀና ምላሽ መስጠት እንደሚጠበቅበት የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍፁም አሰፋ ተናገሩ።

ኮሚሽነሩ ከሲዳማ ክልል አመራሮችና ባለሀብቶች ጋር ገበታ ለሀገር የልማት ፕሮጀክት ዙሪያ ተወያይተዋል።

በውይይቱ ወቅት እንዳሉት  ገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ለዐይን ዕይታ ከመማረክ ባለፈ እንደ ሀገር በርካታ አንድምታዎች አሏቸው።

ያለንን ውስን ሀብት በማሰባሰብ በራስ አቅም ትላልቅ ኢኮኖሚ ማመንጨት የሚችሉ ሥራዎችን ዕውን በማድረግ ህዳሴያችንን ለማረጋገጥ ያስችላል ብለዋል።

በፕሮጀክቶቹ ሥራ ላይ የሚሳተፉ ባለሀብቶችንና በሥራቸው ተቀጥረው የሚሰሩ በርካታ ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ እንደሆነ ገልፀው ከተጠናቀቁም በኋላ የቱሪዝም ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ በማነቃቃት የሀብት ምንጭ እንደሚሆኑ ገልጸዋል።

አሁን ላይ በሶስት ክልሎች የታቀዱት ፕሮጀክቶች በሂደት ወደ ሌሎች  ክልሎችም እንደሚሸጋገሩ የጠቆሙት ኮሚሽነሯ ለቀረበው የ“ ገበታ ለሀገር ” ሀገራዊ ጥሪ ሁሉም ሰው ቀና ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ  የሚጠበቅበት መሆኑን ተናግረዋል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው ፕሮጀክቶቹ ካላቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ባሻገር ሀገርን እንዴት በጋራ መገንባት እንደምንችል ያየንበት ነው ብለዋል።

የለውጡ አመራር ካሁን በፊት በትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ የተለመደውን ኋላ ቀር የአመራር ብልሹነት አመለካከት የሰበረ እንደሆነም ተናግረዋል።

ቤተ-መንግስቱን በማደስ የተጀመረውና በአጭረ ጊዜ ውስጥ የሸገርና፣እንጦጦ ፕሮጀክቶችን በጥራት በማከናወን ያሳየን የለውጡ ኃይል ከተባበርን እንዴት አካባቢያችንን መለወጥ እንደምንችል ያመላከተ ነው ያሉት ደግሞ  የሲዳማ  ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ናቸው።

ለፕሮጀክቱ ጥሪ ተገቢ ምላሽ መስጠት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ መድረኩም የተዘጋጀው የክልሉ አመራርና የባለሀብቱን ተሳትፎ ለማቀናጀት እንደሆነ ተናግረዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ መላኩ አበራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመላው ህዝብ ያቀረቡት ጥሪ  በመሆኑ በጎ ምላሽ መስጠት ይጠበቅበናል ብለዋል።

ይህ ፕሮጀክት እንደ ሀገር ትልልቅ ጉዳዮችን ማቀድ ብቻ ሳይሆን መፈፀም እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ጠቁመው ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት በግላቸው 500 ሺህ ብር ለማበርከት ቃል ገብተዋል።

አቶ ዘሪሁን ቃሚሶ የተባሉ ባለሀብት በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ሀገርን በጋራ ለመገንበት ወሳኝ በመሆኑ የበኩላቸው  ድጋፍ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም