ቀጥታ፡

በአፋር ክልል በጎርፍ ለተጎዱ ወገኖች ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ምግብና ቁሳቁስ ተሰበሰበ

ሰመራ፣ ነሐሴ 23/2012(ኢዜአ) በአፋር ክልል ጎርፍ ጉዳት ላደረሰባቸው ወገኖች ከ80ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ልዩ ልዩ ምግብና ቁሳቁስ በድጋፍ መሰብሰቡን የክልሉ አዴጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ከአማራ ደቡብ ወሎ ዞንና ኦሮሚያ  አዳማ ከተማ ትናንት የተለያየ ምግብና አልባሳት ድጋፍ ተደርጓል።

በዚህ ወቅት የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን እንደተናገሩት በክልሉ በተከሰተው ጎርፍ የተጎዱ ወገኖችን ለመደገፍ ኢትዮጵያዊያን ከጎናቸው በመቆም አብሮነታቸውን በተግባር አሳይተዋል።

ክልሉ ከተለያዩ አጋሮች ያገኘው ድጋፍና ያለውን ክምችት በመጠቀም ዘርፉ የሚመራበትን የአሰራር ስርዓት ተከትሎ ለተጎጂ ወገኖች የእለት ደራሽ ምግብና ምግብ-ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን በአግባቡ እያደረሰ ነው ብለዋል።

ሆኖም ባለፈው ሳምንትም በክልሉ በመካከለኛው አዋሽ ስር በሚገኙ ወረዳዎች ጎርፍ በመከሰቱ  የተጎጂዎቹ ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

ይህን ሆኖ እስካሁን በክልሉ ከ17ሺህ ኩንታል በላይ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን ጨምሮ ከተለያዩ  የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመጡ አካላት የተሰበሰበው  ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት አቶ መሐመድ አስታውቀዋል።

በክልሉ መንግስትና ተጎጂዎች ስም ሁሉንም ኢትዮጵየዊያን ላሳዩት አጋርነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ከእለት ደራሻ እርዳታ በተጓዳኝ ክልሉ መንግስታዊና መንግሰትታዊ ያልሆኑ አጋር ድርጅቶችን በማስተባባር ተጎጂዎቸን በዘላቂነት ለመቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ኩልሱማ ቡርሃባ በበኩላቸው ከተለያዩ አካላት የሚመጣው ድጋፍ ለተጎጂዎቹ እንዲደርስ ከማድረግ በተጓዳኝ በተለይም የተፈናቀሉትን ለጎርፍ በማያጋልጥ ቦታዎች  መልሶ ለማቋቋም  እየተሰራ ነው ብለዋል።

ትናንት ድጋፍ ካደረጉት መካከል የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሰኢድ መሐመድ እንደገለጹት የአፋርና ወሎ ህዝቦች በደምና በባህል የተሳሰሩ ጎረቤት ብቻም ሳይሆን ቤተሰብ  ናቸው።

ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ ማድረጋቸው አብሮነታቸውንና ወንድማማችነታቸን ለማሳየት እንደሆነ ገልጸው በቀጣይም ለመደገፍ ቃል ገብተዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሁሴኒ መሐመድ በበኩላቸው ከንግዱ ማህብረሰብና ሌሎች አካላን  አስተባበሮ ያሰባሰቡት ከ350 ኩንታል በላይ ዱቄት ይዘው መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ድጋፋቸውን ተጎጂዎቹ ወደ መደበኛ ኑሯቸው እስኪመለሱ ተጠናክሮ እንደሚቀጠል ገልጸዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም