ቀጥታ፡

የሃይማኖት ተቋማት የሚጠበቅባቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23/2012 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጾታዊና አካላዊ ጥቃት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሃይማኖት ተቋማት ሚናቸውን እንዲወጡ ጠየቀ።

የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጾታዊና አካላዊ ጥቃት ለመከላከል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት የሃይማኖት ተቋማት ተሰሚነታቸውን በመጠቀም በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በመከላከል በኩል ሚናቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የደቀነውን አደጋ ከመከላከል ጎን ለጎን ተቋማቱ በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊና አካላዊ ጥቃትን ከመቃወም ባለፈ አስከፊነቱን ሊያስተምሩ ይገባል ብለዋል።

መድረኩ በቀጣይ በአዲስ አበባ በአሥሩም ክፍለ ከተሞችና ችግሮቹ ጎልተው በሚታዩባቸው የተመረጡ ክልሎች እንደሚካሄድም ቀሲስ ታጋይ ጠቁመዋል።

የዛሬው መድረክም በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጾታዊና አካላዊ ጥቃት በመከላከል በኩል የእምነት አባቶችና ተቋማት በሚኖራቸው ሚና ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።

  

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የእምነት ተቋማት በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃት አስከፊነትና የሚያስከትለውን ጉዳት ለእምነቱ ተከታዮች ተከታታይ ትምህርት መስጠት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ተከታዮቻቸውን በሥነ ምግባር በማነጽ በከል የሃይማኖት ተቋማት አስተዋጿቸው የጎላ መሆኑን ጠቁመው፣ በርካታ አማኞች በሚኖሩበት አገር በሴቶች ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጾታዊም ሆነ አካላዊ ጥቃት ሊወገዝ እንደሚገባም አመልክተዋል።

በቀጣይ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ ማውጣት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሃይማኖት አባቶችም ተከታዮቻቸውን ቀጣይነት ያለው ትምህርት በመስጠት በአግባቡ ማነጽ እንደሚገባም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም