በቦሌ ለሚ ኢንደስትሪ መንደርና አካባቢው የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለመቀጠል ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በቦሌ ለሚ ኢንደስትሪ መንደርና አካባቢው የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለመቀጠል ጥረት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 23/2012(ኢዜአ) በቦሌ ለሚ ኢንደስትሪ መንደርና አካባቢው የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለመቀጠል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ ሃይል አስታወቀ።
የክረምቱ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ በቦሌ ለሚ ኢንደስትሪ መንደር አካባቢ አንድ ባለ 132 ኪሎ ቮልት ኃይል ተሸካሚ ምሰሶ በመውደቁ ከነሐሴ 21 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው ሃይል መቋረጡ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የህዝብና ዓለም ዓቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢዜአ እንደገለጹት የተቋረጠውን የኤሌክትሪክ ሃይል ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ ነው።
የወደቀውን የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶ በሌላ የመተካት ስራው ጊዜ የሚወስድ በመሆኑ የአካባቢው መስመር ከኮተቤ ከሚወጣ መስመር ጋር በጊዜያዊነት በማገናኘት ዛሬ ማምሻውን ኃይል እንዲያገኝ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
ሆኖም አሁንም እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ ስራውን እያስተጓጎለ ስለመሆኑ ዳይሬክተሩ ገልጸዋለ።
መስመሩን አገናኝቶ ሃይል ለመልቀቅ የሚከናወናው ስራ ትናንት ማምሻውን ለማጠናቀቅ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም በወቅቱ በጣለው ከባድ ዝናብና ማጠናቀቅ ሳይቻል ቀርቷል።
በዛሬው እለት ግን መስመሩ ተስተካክሎ አካባቢው የኤሌክትሪክ ሃይል እንደሚያገኝ አረጋግጠዋል።
በቦሌ ኢንዱስትሪ መንደርና አካባቢው ሰኔ ወር 2012 ዓ.ም አጋማሽ ላይ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ በዘራፊዎች ተፈቶና ተቆርጦ በመውደቁ በአካባቢው ኃይል ተቋርጦ እንደነበር የሚታወስ ነው።