ቀጥታ፡

ሕብረተሰቡ ከግድቦች በሚለቀቀው ውሃ ጉዳት እንዳይደርስበት አየተሰራ መሆኑን ባለስልጣኑ ገለጸ

አዲስ አበባ ነሐሴ 22/2012 ዓም (ኢዜአ) ሕብረተሰቡ እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ  ከግድቦች በሚለቀቀው ውሃ ጉዳት እንዳይደርስበት ጥንቃቄ እንዲያደርግ የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን ገለፀ።

በጎርፍ ምክንያት በግድቦች አካባቢ ባሉ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የቅድመ ጥንቃቄ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑም ተጠቁሟል።

የባለሰልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነች ያሬድ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጹት በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ግድቦች ከአቅም በላይ ውሃ በመያዛቸው የማስተንፈስ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው።

የማስተንፈስ ሥራ ከሚሰራባቸው ግድቦች ውስጥ የቆቃ ግድብ ከአቅም በላይ ውሃ በመያዙ ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በአዋሽ መልካሳ፣በወንጂና በመተሐራ አካባቢ ባሉ ወንዞች ዙሪያ የሚኖረው ሕዝብ ለማንሳት  ከሚመለከተው አካል ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።

የጣና በለስ ግድብ ከአቅሙ በላይ የሆነውን ውሃ ስለሚለቅ በፎገራና ደምቢያ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች መነሳት እንዳለባቸው ዋና ዳይሬክተሯ አመልክተዋል።

የጊቤ ሶስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ከፍተኛ ውሃ በመያዙ የሚያስከትለውን ጎርፍ ለመከላከል የጥንቃቄ ሥራዎች በመካሄድ ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

የከሰም ግድብም ከመጠን በላይ በመሙላቱ  በመካከለኛው አዋሽ አካባቢ የጎርፍ አደጋ ስጋት መኖሩን ዶክተር አዳነች አስታውቀዋል።

የተንዳሆ ግድብም በከፍተኛ ሁኔታ በመሞላቱ በግድቡ የታችኛው አዋሽ አካባቢ የጎርፍ ስጋት መኖሩን አስረድተዋል።

የክረምቱ ዝናብ ተጠናክሮ ከመቀጠሉ በፊት በግድቦች አካባቢ ያለውን ማሕበረሰብ በማንሳት አደጋዎችን መቀነሳቸውን ጠቅሰዋል።

በላይኛው አዋሽ፣ በምዕራብና ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞኖች ጎርፍን በመከላከል ከ18ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ከአደጋ  መዳናቸውን አመልክተዋል።

በአገሪቱ ካሉት ከ 11ዱ ግድቦች መካከል የመልካ ዋከና፣የግልገል ጊቤ አንድ፣ፊንጫ፣አመርቲነሽና ገናሌ ዳዋ  ግድቦች ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የጎርፍ አደጋ ይደርስባቸዋል ተብሎ እንደማይገመትም ጠቅሰዋል።

እንደ ዶክተር አዳነች ገለፃ በአሁኑ ወቅት የክረምቱ ዝናብ በመጠናከሩ አመሻሽ ላይ ከፍተኛ ዝናብና ጎርፍ ስለሚኖር በንቃት መከታተል እንደሚያስፈልግም  ጠቁመዋል።

በነዚህ ዓመት በአገሪቱ የጣለው ከፍተኛ ዝናብ በአንዳንድ ቦታዎች በ100 ዓመታት፤ በሌሎች ደግሞ ከ30 ዓመታት አንዴ መከሰቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም