የአዲስ አበባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ ጥቃት አወገዘ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ ጥቃት አወገዘ
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 22/2012 ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሴቶች ላይ እየደረሰ የሚገኘውን ጾታዊና አካላዊ ጥቃት አወገዘ።
ጉባኤው በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን ጾታዊና አካላዊ ጥቃት በተመለከተ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጓል።
የአዲስ አበባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሰብሳቢ ፓስተር ታምራት አበጋዝ በውይይቱ ወቅት እንደገለጹት፤ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የፈጠረውን አስቸጋሪ ሁኔታ ለመሻገር አማኞች በተለያዩ በጎ-ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ ነው።
በዚህም የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውን ማስመስከራቸውን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ ከዚህ የበጎ ስራ በተቃራኒ አንዳንድ ወገኖች ፈጣሪን የሚያስቆጣ ድርጊት እየፈጸሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በተለይም በአዲስ አበባ እና በአንዳንድ የክልል ከተሞች ውስጥ ጾታዊና ተዛማጅ የቤት ውስጥ ጥቃቶች እየተፈጸሙ መሆኑን ጠቁመዋል።
የጥቃቱ ሰለባዎችም ሆኑ ፈጻሚዎች በቅርብ የቤተሰብ አባላት መሆናቸው ደግሞ ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።
ድርጊቱ በኃይማኖት አስተምህሮ የተወገዘ መሆኑን ሁሉም ኃይማኖቶች የሚያስተምሩትና አጸያፊ ተግባር እንደሆነም ፓስተር ታምራት ተናግረዋል።
የኃይማኖት ተቋማት ይህንን እኩይ ተግባር ከማውገዝ ባለፈ ለመንፈስ ልጆቻቸው ቀጣይነት ያለው ትምህርት በመስጠት እና በመከላከል የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ በእንደዚህ አይነት ተግባራት የተሳተፉ አካላት አስተማሪ የሆነ ቅጣት ማግኘት እንዳለባቸው በመግለጽ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
መሰል ተግባሮችንም ማውገዝ የእለት ተእለት ሥራ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።
የሃይማኖት አባቶቹ በኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ድርጊት መፈጸሙ የስነ ምግባር ትምህርት በስፋት መስጠት የሚያስፈልግ መሆኑን እንደሚያመላክት ገልጸዋል።