ቀጥታ፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ የአገር ምርት የሚተዋወቅበት መርሃ ግብር ይካሄዳል

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 22/2012 ( ኢዜአ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ለአንድ ወር የሚቆይ የኢትዮጵያን የዕደ ጥበብ ውጤቶች የሚተዋወቁበት መርሃ ግብር ሊካሄድ መሆኑን አዘጋጆቹ አስታወቁ።
መርሃ ግብሩን ያዘጋጀው ዱናሚ ሶሻል ኢንተርፕረነር ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ከባህልና ቱሪዝምና ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴሮች ጋር በመሆን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የማህበሩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ የተማረ አወቀ እንደገለጹት ''የኢትዮጵያ ምርት ቀን ምርጥ ቀን'' በሚል መሪ ሃሳብ  መርሃ ግብሩ ተዘጋጅቷል።

 ከነሐሴ 27/2012 እስከ መስከረም 20/2013 በሚቆየው መርሃ ግብር በአገር ባህል አልባሳት ላይ የባለቤትነትና የእኔነት ስሜትን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን አስረድተዋል።

በመጀመሪያው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የመንግሥት ባለሥልጣናት የባህል ልብስ የማልበስና የማስተዋወቅ ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።

በቀጣዮቹ ሳምንታትም እንዲሁ ከጎዳና ተዳዳሪ የማህበረሰብ ክፍሎች ጀምሮ፣ሴቶች፣ወጣቶችንና ህጻናትን የማልበስ ተግባር እንደሚከናወን ገልጸዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተካ ገብረየስ ህብረተሰቡ የባህል አልባሳትን በመልበስና በማስተዋወቅ አገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

መርሃ ግብሩ በኮቪድ-19 ምክንያት የተቀዛቀዘውን የአልባሳቱን የማምረት ሂደትንና አምራቾችን እንደሚያነቃቃ ተናግረዋል።

የዕደ ጥበብ አምራቾች ባሉበት ሆነው የገበያ ትስስርና የልምድ ልውውጥ  መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር  እምነታቸውን ገልጸዋል።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የእደ ጥበብ ማበልጸግ ገበያ ልማት ዳይሬክተር አቶ ነጋሽ አሰፋ እንዲሁ መርሃ ግብሩ የአገሪቱ የባህል መገለጫ የሆነውን አልባሳትና የእደ ጥበብ ውጤት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያስተዋውቃል ብለዋል።

በተለይም መርሃ ግብሩ  እውቅ ሰዎችን በባህል አልባሳት እንዲታዩ በማድረግ አገሪቱ ያላትን ቱባ ባህል ለማስተዋወቅ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

 የሥራ ፈጠራን የሚያበረታታና የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረት አንጻር ፋይዳው የጎላ  መሆኑን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በእደ ጥበብ ሙያ መሰማራታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም