ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ለአባይ ተፋሰስ አገሮች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ትምህርት የሰጠ ነው- አምባሳደሮች

 አዲስ አበባ ነሐሴ 22/2012 ዓም (ኢዜአ)ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገንባት ለአባይ ተፋሰስ አገሮች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም ህዝባቸውን ከድህነት ለማስወጣት ትምህርት የሰጠ መሆኑን አምባሳደሮች ተናገሩ።

በአባይ ተፋሰስ አገራት የኢትዮጵያ አምባሳደሮች ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአባይ ለተፋሰስ አገሮች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ያመላከተ መሆኑን አንስተዋል።

በኡጋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር አለምጸሃይ መሰረት እንዳሉት ኢትዮጵያ ግድቡን በመገንባት ያሳየችው የፍትሃዊ ተጠቃሚነት አካሄድ ለተፋሰሱ አገሮች ህዝባቸውን ከድህነት ለማስውጣት ትምህርት ሰጥቷል።

የግድቡ መገንባት በተለይም ለላይኞቹ የተፋሰሱ አገሮች ሁለት ወሳኝ ነጥቦችን አስተምሮ ያለፈ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤትና ከሌሎች የተፋሰሱ አገሮች ጋር በጋራና በትብብር የመጠቀም አቋም አንደኛው መሆኑን ያብራሩት አምባሳደር አለምጸሃይ የአፍሪካ አገሮች የሃይል አቅርቦትን ጨምሮ ዝቅተኛ የሆነውን መሰረተ ልማታቸውን ለማሻሻል ልምድ የሚያጋራ ነው ብለዋል።

አፍሪካዊያን ከድህነት ለመውጣት ግዙፍ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በራሳቸው አቅም መስራት እንደሚችሉም ግድቡ አሳይቷል ብለዋል።

በሩዋንዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሉሊት ዘውዴ በበኩላቸው የህዳሴ ግድብ ቀጣናዊ ትብብርና ልማትን የሚያመጣ የጋራ ፕሮጀክት መሆኑን ለሩዋንዳውያን ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።

እየተካሄደ ያለው የግድቡ ድርድር በሰላማዊ መንገድ ተጠናቆ ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ ላይ አወንታዊ እይታ አላቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ ሃብቶችን በጋራና ትክክለኛ በሆነ መንገድ ከጎረቤት አገሮች ጋር ተጠቃሚ ለመሆን ባላት አቋም የናይል የትብብር ማዕቀፍ ሲመሰረት ጀምሮ አባል አገር ናት።

ኮሚሽኑን ለመመስረት ከሚጠበቀው ስድስት አገሮች መካከል ኢትዮጵያን ጨምሮ ሩዋንዳና ኡጋንዳ ስምምነቱን ካጸደቁ 4 አገሮች ውሰጥ ይገኛሉ።

ሩዋንዳና ኡጋንዳ የተፋሰሱ አገሮች የጋራ ሃብት የሆነው የአባይ ወንዝ ትክክለኛ በሆነ መንገድ የመጠቀም አቋም እንደሚያንጸባርቁም አምባሳደሮቹ ገልጸዋል።

የአባይ ወንዝ 6 ሺህ 650 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሁን ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 የተፋሰሱ አባል አገሮች መኖራቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም