በአማራ ክልል የፊትና አፍንጫ ጭንብል ማድረግን የሚስገድድ ዘመቻ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የፊትና አፍንጫ ጭንብል ማድረግን የሚስገድድ ዘመቻ ተጀመረ
ባህር ዳር ነሐሴ 22/2012 ኢዜአ በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ ሰርጭንት ለመከላከል ሁሉም ሰው የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል እንዲያደርግ የሚያስገድድ የአንድ ሳምንት ዘመቻ ዛሬ ተጀመረ።
የክልሉ ኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ዛሬ በሰጠው መግለጫ ዘመቻው ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ነው።
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ደረጃ የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊና የክልሉ የኮሮና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ዶክተር ሙሉነሽ አበበ በሰጡት መገለጫ ዘመቻው በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች ዛሬ ተጀምሯል።
ዘመቻው በክልሉ ማንኛውም ሰው የፊትና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ሳያደርግ መንቀሳቀስ እንደማይችል የወጣን አስገዳጅ መመሪያ ማስተግበር አላማ ያደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።
የኮሮና ቫይረስ እሰኪጠፋ ድረስ ህብረተሰቡ ጭንብል የማድረግ ባህልን አጠናክሮ እንዲቀጥል ማስቻልም የዘመቻው አላማ መሆኑን አመላክተዋል።
በዘመቻው በኃይማኖት ተቋማት፣ በትራንስፖርት፣ በገበያ ስፍራዎችና ንግድ ተቋማት ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰዋል ።
"ለአንድ ሳምንት በሚቆየው ዘመቻ ሁሉም ሰው ጭንብል ሳያደርግ እንዳይንቀሳቀስና በማንኛውም ተቋም አገልግሎት እንዳያገኝ ይገደዳል" ብለዋል ።
እንደ ዶክተር ሙሉነሽ ገለጻ በዘመቻው በየደረጃው የሚገኝ የክልሉ የፀጥታ ኃይልና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ቅንጅት በመፍጠር ህግ የማስከበር ስራቸውን በብቃት ይወጣሉ።
የክልሉ የሰላምና የህዝብ ደህንነት ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮማንደር መንገሻ አውራሪስ በበኩላቸው በሽታውን ለመከላከል የወጡ ህጎችን የፀጥታ ኃይሉ እንዲያስከብር አስፈላጊው ስምሪት መሰጠቱን ተናግረዋል ።
የፀጥታ መዋቅሩ የተሰጠውን ህግ የማስከበር ስራ በአግባቡ እንደሚወጣ የገለጹት ኮማንደር መንገሻ ህዝቡ የፀጥታ አካሉን በማገዝ ለህጉ ተግባራዊነት የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል ።
ዛሬ በባህር ዳር በተጀመረው ዘመቻ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገርን ጨመሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች የተገኙ ሲሆን በማርሽ ባንድ የታገዘ የጎዳና ትርኢት ተካሂዷል ።