ቀጥታ፡

አርሶ አደሩ ከቡናው የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝና የመሰረተ ልማት ችግሮቹን ለማቃለል እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 22/2012 ( ኢዜአ) አርሶ አደሩ ላመረተው ቡናው የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝና የመሰረተ ልማት ችግሮቹን ለማቃለል እየሰራ መሆኑን ቀርጫንሼ ትሬዲንግ የተባለ ኩባንያ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣንና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በምዕራብ ጉጂ ዞን ቡሌ ሆራ ወረዳ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግባቸውን እንቅስቃሴ አስጎብኝቷል፡፡ 

የቡሌ ሆራ ወረዳ አንዳንድ ቡና አምራች አርሶ አደሮች ድርጅቱ ለልፋታቸው ተመጣጣኝ  ዋጋ እየከፈላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቡና ስራ ከፍተኛ ጉልበት የሚጠይቅ ነው ያሉት አርሶ አደሮቹ ፤ ድርጅቱ ወደ አካባቢያቸው ከመግባቱ በፊት ልፋታቸውና የሚያገኙት ጥቅም ተመጣጣኝ እንዳልነበር ይናገራሉ።

ከዚህ ቀደም አንድ ኪሎ ግራም ቀይ ቡናን ከ 2  ብር  ከ 50 ሣንቲም እስከ 5 ብር ይሸጡ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ ወደ አካባቢያቸው ከመጣ በኋላ ግን አንድ ኪሎ ግራም ቀይ ቡናን ከ17 አስከ 18 ብር በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በበጋው ወቅት ላይ ባቀረቡት ቡና መጠን አርሶ አደሩ ገንዘብ በሚያጣበት  በክረምት ወቅት የማበረታቻ ተጨማሪ ክፍያ በመስጠት ድጋፍ እያደረገልን ነው ብለዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ እንዳሉትም ድርጅቱ በአካባቢያቸው የመሠረተ ልማት ተቋማትን እየዘረጋላቸው ነው፡፡

ይህም ትምህርት ቤት ፣ ንጹህ መጠጥ ውሃ ፣ የጠጠር መንገድን እንደሚያካትት ጠቁመዋል፡፡  

የቀርጫንሼ ትሬዲንግ ኩባንያ ማኔጂንግ ዳይሬክተርና ባለቤት አቶ እስራኤል  ደገፍ ለአርሶ አደሩ የሚመጥን በጎ ተግባር ማድረግ ግዴታ እንጂ፤ ስጦታ አይደለም  ብለዋል፡፡

ባለሃብቶች ካፒታላቸውን ከማሳደግ ባለፈ ፤ህብረተሰቡን መጥቀም እንደሚኖርባቸው  አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር  አቶ ሣህለ ማርያም ገብረ መድህን እንዳሉትም አልሚዎች በሁሉም ዘርፎች የሚገኙበትን አካባቢ እንዲያለሙና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ  የሚያደርግ መመሪያ መኖሩን ገልጸዋል፡፡

ኩባንያው እያከናወነ የሚገኘው ተግባርም እንደሚደነቅ ገልጸው፤ ሌሎች ባለሀብቶች  ልምዱን እንዲቀስሙ አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም