በአዲሱ ዓመት ለ10 የኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙኃን ፈቃድ ሊሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲሱ ዓመት ለ10 የኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙኃን ፈቃድ ሊሰጥ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 22/2012 ( ኢዜአ) በአዲሱ ዓመት ለአስር የኤሌክትሮኒክስ የመገናኛ ብዙኃን ፈቃድ እንደሚሰጥ ብሮድካስት ባለስልጣን አስታወቀ።
መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ኢንዱስትሪውን አትራፊ ለማድረግ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ ለኢዜአ እንደገለጹት በቀጣዩ ዓመት በኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙኃን ዘርፍ ፈቃድ ይሰጣል።
ፈቃዱን ከሚያገኙት መካከል በጨረታ ያሸነፉ ሶስት ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ይገኙበታል።
እንዲሁም ማስረጃዎችን አሟልተው የቀረቡ የሳተላይት ጣቢያ ፈቃድ ፈላጊዎች ወዲያውኑ ይስተናገዳሉ።
ፈቃዱ የሚሰጠው ፍላጎትን በማመጣጠንና ያለውን ምጥን የሆነውን የአየር ሞገድ ታሳቢ በማድረግ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
የሕትመት መገናኛ ብዙኃን ለማስፋፋት ፍላጎትን መሰረት አድርጎ ፈቃድ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነውም ብለዋል።
ዘርፉ አዋጭና ተመራጭ ኢንዱስትሪ ሆኖ ለአገር እድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለማድረግ እንደሚሰራም ዶክተር ጌታቸው አመልክተዋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በገለልተኝነት እንዲሰሩ የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንደሚደረግ ነው የገለጹት።
በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን የሚስተዋለውን ያልተገባ አካሔድን በማስከን ዘርፉን ወደፊት በማራመድ ረገድ በኃላፊነት ስሜት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
መገናኛ ብዙኃን በብዝኃነት ውስጥ ያለው አንድነት ለማጠናከርና አካሔዳቸውን በማስተካከል ሕብረተሰቡን የሚያገለግሉበትን አሰራር ለመዘርጋት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በቅርቡ የፀደቀው የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ በመገናኛ ብዙኃን መስክ ከውጭ ለሚመጣ ኢንቨስትመንት ክፍት ማድረጉን ዶክተር ጌታቸው ገልጸዋል።
ይሕም የዘርፉን ኢንቨስትመንት ለማሳደግና አዋጭ በሆነ መንገድ ባለሙያዎች ስነ ምግባር አክብረው እንዲሰሩ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ዶክተር ጌታቸው እንዳሉት በአሁኑ ወቅት መገናኛ ብዙኃን በከተሞች ብቻ ገበያ ተኮር ሆነው የሚሰሩበት ሁኔታ ያለ ሲሆን በቀጣይ መንግሥት ለኢንዱስትሪው ማበረታቻ በማድረግ ተደራሽነታቸውን ለማስፋት እየሰራ ነው ።
ይሕም የመገናኛ ብዙሃን ብዝሐነትን፣ፍትሐዊነትና መረጃን ተደራሽ ለማድረግና በዚህም ላይ ተመስርቶም በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተሳትፎአቸውን እንደሚያሳድገው ዋና ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።
ባለስልጣኑ በዚህ ዓመት ለሶስት የኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ፖሊሲ ነሐሴ 16 ቀን 2012 በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁ ይታወቃል።