የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ቀጣይነት እንዲኖረው የዲፕሎማሲ ጥረቱ ቀጥሏል- አምባሳደር ሽፈራው - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ቀጣይነት እንዲኖረው የዲፕሎማሲ ጥረቱ ቀጥሏል- አምባሳደር ሽፈራው
አዲስ አበባ ነሐሴ 22/2012 ዓም (ኢዜአ) በአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ሲሪል ራማፎዛ መሪነት የሚካሄደው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ቀጣይነት እንዲኖረው የዲፕሎማሲ ጥረቱ መቀጠሉን በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ገለጹ።
አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያም ለኢዜአ እንደተናገሩት የአፍሪካን ችግር በአፍሪካውያን ለመፍታት የሚደረገው ድርድር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ የሚደረገው ድርድር ቀጥሏል።
በፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ የሚመሩት የሶስትዮሽ ድርድር የግድቡ የውሃ ሙሌትና አስተዳደር ቀጣይነት እንዲኖረው ጥረቱን ቀጥሏል ብለዋል።
ድርድሩ የፕሬዚዳንቱ የህብረቱ ሊቀመንበርነት ሲያበቃ መንበሩን የሚረከበው መሪ እንዲያስቀጥለው እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል ።
የህብረቱ ሊቀመንበር ሥልጣን የሚቆየው ለአንድ ዓመት በመሆኑ የኢትዮጵያን ፍላጎትና ለአፍሪካውያን ያለውን ፋይዳ ማስረዳት ቀጣይነት ያለው ስራ እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
የግድቡ ጉዳይ የኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፤ የተፋሰሱ አገሮች ጭምር በመሆኑ ፕሬዚዳንቱ በሊቀመንበርነት ዘመናቸው ድርድሩን ለማጠናቀቅ ውይይቱ እየተካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
እንደ አምባሳደሩ ገለጻ ደቡብ አፍቲካ በአንድ በኩል ሰብሳቢ በሌላ መንገድ ታዛቢ በመሆኗ አዳዲስ መረጃ እየተለዋወጡ ነው።
ኤምባሲው ኢትዮጵያ የግድቡን ግንባታን ዓለም አቀፍ መርሆዎችን ተከትላ እየገነባች መሆኑን እያስረዳ መሆኑን ገልጸዋል።
በደቡብ አፍሪካና አካባቢው የሚገኝ የኢትዮጵያ ማህበረሰብም የኢትዮጵያን ምክንያታዊና ፍትሃዊ አቋም እያስረዳ መሆኑንም አምባሳደር ሽፈራው አስታውቀዋል።
በዚህም ከ350 በላይ የሙያና ሌሎች አካላትን ያሰባሰበና በደቡብ አፍሪካ ተሰሚነት ያላቸውን መገናኛ ብዙኃን በመጠቀም እየሰራ ነው ብለዋል።
የግድቡ የመጀመሪያው ዙር ውሃ ሙሌት በደቡብ አፍሪካና አካባቢዋ በሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ዘንድ ሃሴት መፍጠሩን ተናግረዋል።
በዚህም ፕሮጀክቱን በዲፕሎማሲና ሃብት ማሰባሰብ ለመደገፍ በደቡብ አፍሪካ፣ ሞዛምቢክ፣ ቦትስዋና፣ ሌሴቶና በአካባቢው አገሮች እንቅስቃሴ በመደረግ ላይ እንደሚገኝ አምባሳደር ሽፈራው አስረድተዋል።