የኢትዮ-ቻይና ወዳጅነት የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል-ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ

64
አዲስ አበባ ግንቦት 2/2010 የኢትዮጵያና ቻይና እውነተኛ ወዳጅነትና አጋርነት የበለጠ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል ሲሉ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለጹ። ፕሬዚዳንቱ የቻይና ህዝባዊ ኮንግረስ አፈ-ጉባኤ ሌ ዛን ሹን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው  አነጋግረዋል። ዶክተር ሙላቱ  በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በኢትዮጵያ ውስጥ የኢኮኖሚ እድገት እንዲገኝና መሠረተ ልማቶች እንዲስፋፉ "አገሪቷ ከምትተገብረው የጠራ ፖሊሲና ስትራቴጂ ባሻገር የቻይና እገዛና ድጋፍ ከፍተኛ ነው"። በአዲስ አበባ የተገነባው የቀለበት መንገድ፣ ቀላል ባቡር፣ የአዲስ አበባ -አዳማ ፈጣን መንገድ፣ በተለያዩ ክልሎች የተመሰረቱ የጨርቃ ጨርቅ እና የመሳሰሉት ኢንዱስትሪ ዘርፎች ኢትዮጵያ ከቻይና ድጋፍና እገዛ ካገኘችባቸው ትላልቅ ፕሮጀክቶች መካከል ናቸው። በኢንቨስትመንት መስክም በ624 ፕሮጀክቶች 4 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ኢንቨስት በማድረግ ከመቶ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል እንዲፈጠር ያስቻለው የቻይና መንግስት ያደረገው ድጋፍ ነው። ይህ በአገራቱ መካከል ያለው ቀዳሚና እውነተኛ ወዳጅነትና አጋርነት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነው ፕሬዚዳንቱ የጠየቁት። ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ላላት እውነተኛ ወዳጅነትና አጋርነት ትልቅ ቦታ የምትሰጥ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ፣ ኢትዮጵያ ወደፊትም በተለያዩ መስኮች ከቻይና ጋር ተባብራ ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ጨምረው ገልጸዋል። የቻይና ህዝባዊ ኮንግረስ አፈ-ጉባኤ ሌ ዛን ሹ በበኩላቸው "ቻይና ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍና እገዛ አጠናክራ ትቀጥላለች"። አፈ-ጉባኤ ሌ ዛን ሹ ተመርጠው ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ በአፍሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት ከኢትዮጵያ መጀመራቸው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር  ላላት ወዳጅነትና አጋርነት ትልቅ ትኩረት ለመስጠቷ ማሳያ እንዲሆን ነውም ብለዋል። በተለይም ከአንድ ወር በፊት በኢትዮጵያ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ተደርጎ በአገሪቷ ሰላምና መረጋጋት በመስፈኑ አድናቆታቸውን ገልጸው፤ በቀጣይም በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ተናግረዋል። ኢትዮጵያና ቻይና እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ1970 መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መጀመራቸው መረጃዎች ያወሳሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም