በትግራይ በትራንስፖርት ዘርፍ ኮሮና ለመከላከልል የወጣ መመሪያ በአግባቡ እየተተገበረ አይደለም- ተጠቃሚዎች - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ በትራንስፖርት ዘርፍ ኮሮና ለመከላከልል የወጣ መመሪያ በአግባቡ እየተተገበረ አይደለም- ተጠቃሚዎች
አክሱም ነሐሴ 21/2012ዓም (ኢዜአ) በትግራይ ክልል በትራንስፖርት ዘርፍ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል የወጣ መመሪያ በአግባቡ እየተተገበረ አለመሆኑን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ገለጹ።
መመሪያውን በማያከብሩ ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የክልሉ ኮንስትራክሽን መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል።
የሸራሮ ከተማ ነዋሪ አቶ ድራር ገብረመድህን ለኢዜአ እንደገለጹት በስራ ጉዳይ ወደ አክሱም ከተማ ስለሚመላለሱ በትራንስፖርት ዘርፍ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የወጣ መመሪያ በአግባቡ እየተተገበረ እንዳልሆነ ለመገንዘብ አስችሏቸዋል ።
የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭዎች የተሳፋሪ ቁጥር በግማሽ እንዲቀንሱ የተላለፈን መመሪያ በመጣስ ከመቀመጫ ውጭ ትርፍ በመጫን ህብረተሰቡን ለቫይረሱ ተጋላጭ እያደረጉት መሆኑን ተናግረዋል ።
“የትራንስፖርት ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች ከመንግስት መመሪያ ውጭ በተቃራኒው የሚሰሩበት ሁኔታ አልገባኝም” ያሉት አቶ ድራር በዘርፉ ጠንካራ ቁጥጥርና ክትትል ሊደረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል ።
“በትራንስፖርት ተሽከረካሪዎችና በመናኸሪያዎች ከፍተኛ የሰዎች መተፋፈግና ንክኪ አለ” ያሉት ደግሞ የአክሱም ከተማ ነዋሪ አቶ ጸጋይ ታደሰ ናቸው።
በመናኸሪያዎች መግቢያና መውጫ በሮችም የእጅ መታጠቢያ ጨምሮ ንጽህና ለመጠበቅ የሚያገለግል ምንም አይነት አማራጭ አለመኖሩን ተናግረዋል ።
ከአክሱም መቀሌ መስመር የህዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አሽከርካሪ ወጣት አብረሀየለይ አማረ በበኩላቸ በትራንስፖርት ዘርፍ ያለው መዘናጋት ለቫይረሱ ስርጭት መጨመር የራሱ አስተዋፆ እንዳለው ገልጻል ።
“ኮሮና ቫይረስ መከላከል የወጣ አዋጅ የተላለፉ አሽከርካሪዎች በእስርና በገንዘብ እንዲቀጡ እየተደረገ ነው” ያሉት ደግሞ የትግራይ ማዕከላዊ ዞን የትራፊክ ፖሊስ አስተባባሪና የኮሮረና ቫይረስ መከላከል ግብረ ኃይል አባል ኮማንደር ምሕረተአብ ገብረመድህን ናቸው።
ባለፈው አንድ ወር ብቻ መመሪያውን ተላልፈው የተገኙ 38 አሽከርካሪዎች መቀጣታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።
በትራንስፖርት ዘርፍ የተሰማሩ አካላትም ሆኑ ተጠቃሚዎች የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመከላከል የወጣ አዋጅ ማክበር እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል ።
የትግራይ ክልል ኮንስትራክሽን፣መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሪት ራሄል ኃይሉ በትራንስፖርት ዘርፍ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚረዳ መመሪያ ወጥቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ።
ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች በሁሉም መናኸሪያዎች እንዲኖር የሚያስገድድ ድንጋጌ በመመሪያው መቀመጡን ጠቁመዋል ።
“በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የወጣ መመሪያ በሚተላለፉ ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው” ብለዋል።
በከተማና በወረዳ ደረጃ ያሉ የኮንስትራክሽን መንገድና ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤቶች ደንብና መመሪያ የማስፈጸም ኃላፊነት አለባቸው ያሉት ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በማይወጡ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል ።