ሠራተኞች ለሕይወታቸው ቅድሚያ በመስጠት ራሳቸውን ከኮሮና እንዲጠብቁ ጥሪ ቀረበ - ኢዜአ አማርኛ
ሠራተኞች ለሕይወታቸው ቅድሚያ በመስጠት ራሳቸውን ከኮሮና እንዲጠብቁ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 21/2012(ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል ከባለሙያዎች የሚሰጡ የጥንቃቄ መንገዶችን መተግበር እንደሚገባ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተሰፋዬ አሳስበዋል።
ሚኒስትሯ የኮቪድ-19 የስራ ቦታ ምላሽ ፕሮቶኮል መሰረት "እኔ ሃላፊነት አለብኝ! እናንተስ?" የሚል መልዕክት የያዘ ቢልቦርድ በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ይፋ አድርገዋል።
የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ በተከሰተበት ወቅት የመከላከል ሂደቱ ውጤታማ እንደነበር የጠቀሱት ሚኒስትሯ አሁን የሚስተዋለውን መዘናጋት በማስወገድ ሁሉም ሰው ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
የስራውን ዓለም ደህንነት ከወረርሽኙ ለመከላከል የመንግስት፣ የአሰሪና ሠራተኛ አካላት የስራ ቦታ ምላሽ ፕሮቶኮልና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መመሪያው ወሳኝ ሚና ማበርከታቸውንም ገልጸዋል።
።
ቫይረሱን ለመከላከል የኢትዮጵያ አሰሪዎችና ሠራተኛ፣ ባለድርሻ አካላትና የልማት አጋሮችም ትልቅ ድርሻ ነበራቸው ብለዋል።
ሠራተኞች፣ አሰሪዎችና፣ የስራው ዓለም ተዋንያን በፓርኩ የተተከለውን ቢልቦርድ ልክ እንደ ትራፊክ መብራት በመመልከት ወረርሽኙን የመከላከል ሕጎችን በማክበር እንዲተገብሩም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በበኩላቸው ሠራተኞች በስራ ቦታቸው ያለ መዘናጋት ራሳቸውን ከኮኖና ቫይረስ እንዲጠብቁ መክረዋል።
ሠራተኞች ለሕይወታቸው ቅድሚያ በመስጠት ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ ሊጠብቁ ይገባል ነው ያሉት።