ቀጥታ፡

የኮቪድ-19 ቅድመ መከላከልን በማስመልከት ለሚዲያና ለፍትህ አካላት ስልጠና ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 21/2012(ኢዜአ) ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ የኮቪድ-19 ቅድመ መከላከልን በማስመልከት ለሚዲያና ፍትህ አካላት ስልጠና ሰጠ።

ኮሚቴው ስልጠናውን የሰጠው ከፌደራል ፖሊስ ጋር በመተባበር ነው።

በዚህም ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ቅድመ መካላከል በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ለህብረተሰቡ መረጃ ማድረስ በሚቻልበት ሁኔታ እና ህግ የማስከበር ሂደትን አስመልክቶ ስልጠና ሰጥቷል።

በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ምክትል ኃላፊ ካቲያ ሶሪን እንደገለጹት፣ ስልጠናው የሚዲያና የጸጥታ አካላት ግንዛቤ ኖሯቸው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በቅንጅት እንዲሰሩ የሚያግዝ ነው፡፡

"ሚዲያው የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የጎላ ሚና አለው" ያሉት ምክትል ኃላፊዋ፣ የስልጠናው ተሳታፊዎችም ግንዛቤያቸውን በማሳደግ ህብረተሰቡን በተሻለ እንዲያገለግሉ የጎላ ጠቀሚታ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

በዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ የኮሙዩኒኬሽን ክፍል ኃላፊ አቶ ዘውዱ አያሌው በበኩላቸው፣ "ተሳታፊዎቹ ከስልጠናው በኋላ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተገቢውን ግንዛቤ ይዘው ስራቸውን በተሻለ ለማስኬድ ያግዛቸዋል" ብለዋል፡፡

መገናኛ ብዙሀን የወረርሽኙን የቅድመ መከላከያ መንገዶች ለህብረተሰቡ ተደራሽ እያደረጉ እንደሚገኝ የገለጹት ኃላፊው፣ ስልጠናውም የጸጥታ አካላትን ሥራ እንደሚያግዝ ነው የገለጹት።

የፌደራል ፖሊስ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር መኮንን ጋርጠው እንዳሉት ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ያሰናዳው ስልጠና የጸጥታ አካላት ለህብረተሰቡ እየሰጡት ባለው አገልግሎት የሚያጋጥሙ ክፍተቶችን ለመሙላት ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡

የጸጥታ ኃይሉ የአገርና የህዝብን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለበት ህብረተሰቡን ከኮቪድ-19 ለመከላከል የተለያዩ የህግ ማስከበር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ህብረተሰቡ የጸጥታ አካላት ህግን ለማስከበር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ተባባሪ በመሆን እራሱን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲጠብቅም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የስልጠናው ተሳታፊዎች ስልጠናው ህብረተሰቡ እራሱን ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዲከላከል ተገቢ መረጃ ለማድረስ አጋዥ መሆኑን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በኢትዮጵያ ቅርንጫፉን ከፍቶ ለአርባ ተከታታይ ዓመታት የተለያዩ ሰብአዊ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ተራዕዶ ድርጅት መሆኑን ተመልክቷል።

የቀይ መስቀል ኮሚቴው ከ185 በላይ አገራት የሥራ እንቅስቃሴ በማድረግ በጦርነት እና ብጥብጥ ወቅት ጉዳት ለሚደርስባቸው ሰዎች የህይወት እና ሰብአዊ ክብር ከለላ እንደሚሰጥም ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም