ለግንባታ ባልተፈቀደ መሬት የተገነቡ 162 መኖሪያ ቤቶች መንግሥትን ከ84 ሚሊዮን ብር በላይ አሳጥተዋል - ጽሕፈት ቤቱ - ኢዜአ አማርኛ
ለግንባታ ባልተፈቀደ መሬት የተገነቡ 162 መኖሪያ ቤቶች መንግሥትን ከ84 ሚሊዮን ብር በላይ አሳጥተዋል - ጽሕፈት ቤቱ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21/2012 (ኢዜአ) ለግንባታ ባልተፈቀደ መሬት የተገነቡ 162 መኖሪያ ቤቶች መንግሥት ማግኘት የነበረበትን ከ84 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማሳጣታቸውን የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዐቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
ጽሕፈት ቤቱ እንደገለጸው ቤቶቹ በተለምዶ በክፍለ ከተማው "በርታ" ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የተገነቡ ናቸው።
ቤቶቹ የተገነቡበት 301 ሺህ 563 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው መሬት በ1997 ዓ.ም በወይዘሮ እፀገነት አባተ ሥም ለከብት እርባታ ሥራ እንዲውል ፈቃድ መሰጠቱን የክፍለ ከተማው ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
ቤቶቹ በተለያየ ደረጃና ስፋት የተገነቡ ሲሆን ባለአንድ ፎቅና ከዚያ በላይ ናቸው ተብሏል።
የክፍለ ከተማው ዓቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አስናቀ ረታ እንደገለጹት፣ ግለሰቧ መሬቱን ከተፈቀደው ዓላማ ውጭ ሕጋዊ መንገድን ሳይከተሉ የተሰጣቸውን የከብት እርባታ ፈቃድ ወደ ሪልስቴት በመቀየር 162 ቤቶች እንዲገነቡ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
"እፀገነትና ቤተሰቦቿ ሪልስቴት ዴቨሎፕመንት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር" በሚል ስም ከተገነቡ ቤቶች በአሁኑ ወቅት 152ቱ ለሦስተኛ ወገን መተላለፋቸውንና ቀሪዎቹ ደግሞ በሂደት ላይ መሆናቸውን አቶ አስናቀ አስረድተዋል።
እንደኃላፊው ገለጻ መሬቱ ከከብት እርባታ ወደ ሪልስቴት ሲተላለፍ እንዲሁም ወደ ግለሰቦቹ ወይም ሦስተኛ ወገን በሚተላለፍበት ወቅት መንግሥት ከአገልግሎትና ከቴምብር ክፍያዎች ማግኘት የነበረበትን ከ84 ሚሊዮን 422 ሺህ ብር በላይ አጥቷል።
በክፍለ ከተማው የሕግ ጉዳይ ክርክር ዳይሬክተር አቶ ሉጨ አዳሾ በበኩላቸው፣ ግለሰቧ ከተሰጠው ፈቃድ ውጭ መሬቱን ለሌላ ዓላማ ከማዋል በላይ በ39963 የተመዘገበውን ካርታ ቁጥር ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ አራት እንዲካፈል ማድረጋቸውን አስረድተዋል።
መጀመሪያ ለከብት እርባታ ከተፈቀደላቸው 292 ሺህ 908 ካሬ ሜትር መሬት ቦታ ውጪ ያለአግባብ ተጨማሪ 8 ሺህ 655 ካሬ ሜትር በመያዝ በአጠቃላይ 301 ሺህ 563 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ማኅበሩ የመኖሪያ ቤት ግንባታ መካሄዱን አቶ ሉጨ አስረድተዋል።
ግንባታው የሪልስቴት ሕግጋትን እንዳልተከተለና ክፍለ ከተማው ክትትል በማድረግ የተሰራው ሥራ ተገቢ አለመሆኑን አረጋግጦ በ2010 ዓ.ም ካርታዎቹ እንዲመክኑ ማድረጉን ገልጸዋል።
አቶ ሉጨ እንዳሉት የካርታዎቹን መምከን ተከትሎ የሪልስቴት ባለቤት ወይዘሮ እፀገነት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲከራከሩ ቆይተዋል።
በዚህም ፍርድ ቤቱ በሰበር ሰሚ ችሎት መዝገብ ቁጥር 161979/12 ቦታው ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ የመጨረሻ ውሳኔ መስጠቱንም አቶ ሉጨ ተናግረዋል።
"ከሕግና ሥርዓት ውጭ የሚሆን የለም" ያሉት አቶ ሉጨ፣ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተፈጻሚ ከማድረግ በፊት የአመራሩ ዕውቅናና ውሳኔ እየተጠባበቁ መሆናቸውን አመልክተዋል።