የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኅብረት ጉባዔ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኅብረት ጉባዔ ተጀመረ
አርባ ምንጭ ፣ ነሐሴ 21/2012 (ኢዜአ) 39ኛው የኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ኅብረት ጉባዔ ዛሬ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተጀመረ።
የጉባዔው ዓላማ በመማር ማስተማርና በኮሮና መከላከሉ ረገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሚናን ለማሳደግ በሚቻልበት ዙሪያ ለመምከር መሆኑን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዳምጠው ዳርዛ ገልጸዋል።
በሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፀጥታ ሁኔታ በትምህርት ሥራ ላይ አሉታዊ ጫና እንዳይፈጥር በሚቻልበትም ጉባዔው ይመክራል ብለዋል።
"ተቋማቱ የዕውቀት እንጂ የሥጋት ቀጠና መሆን የለባቸውም" ያሉት ዶክተር ዳምጠው ተማሪዎች ከወትሮው በተለየ ሁኔታ መልካም ስነ-ምግባር ተላብሰው ለመጪው የትምህርት ዘመን መምጣት እንደሚጠበቅባቸውም አስታውቀዋል።
ለዚሁ እውን መሆን የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚዳንቶች በያሉበት ዩኒቨርሲቲ ከተማሪዎችና ማኅበረሰቡ ጋር ተቀራርበው መሥራት አለባቸው ብለዋል።
የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተወካይ ዶክተር ኢዶሳ ተርፌሳ በበኩላቸው ጉባዔው የሥነ ምግባር ጉድለቶችን በማረም በመጪው የትምህርት ዘመን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሥራ የተቃና እንዲሆን የጎላ ፋይዳ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
በተለይ የትምህርት ጥራትና ሥርፀትን በመደገፍ ዩኒቨርሲቲዎች ካሉበት ችግር እንዲወጡም የሚያግዝ ምክከር እንደሚደረግም ይጠበቃል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ከመማር ማስተማርና አገልግሎት ጋር ተያይዞ ችግር ሲገጥማቸው ከቅርብ ተጠሪዎቻቸው ጋር በመመካከር ለዘላቂ መፍትሔ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዚዳንት ተማሪ ኦሊ በዳኔ ሀገራችን የብዝሃነት ተምሳሌት እንደመሆኗ ሁሉም ተማሪ መከባበርና መቻቻል ባህሉ ማድረግ ይኖርበታል ብሏል።
ከሁከትና ብጥብጥ በመራቅ በሚገበየው ዕውቀት ለራሱ፣ ለማኅበረሰቡ ብሎም ለሀገሪቱ ብልፅግና የድርሻውን መወጣት እንደሚጠበቅበትም ገልጿል።
ለዚህ እውን መሆን የተማሪዎችና የኅብረቱ መስተጋብር ወሳኝ እንደሆነም አመልክቷል።