በምሥራቅ አፍሪካ ረሃብና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳያጋጥም የዓለም ምግብ ፕሮግራም አስጠነቀቀ

ነሐሴ 21/2012(ኢዜአ) የዓለም ምግብ ፕሮግራም በምሥራቅ አፍሪካ ረሃብና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳያጋጥም አስጠነቀቀ።

የምግብ እጥረቱ የተከሰተው በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ለጋሽ አካላት አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ ስለቀነሱ መሆኑን አመልክቷል።

በምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች ከባድ ረሃብና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንደሚያጋጥማቸውም የዓለም ምግብ ፕሮግራም በድረ-ገጹ አስፍሯል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ቀድሞ በኢትዮጵያ፣በዑጋንዳ ፣በኬኒያ፣በደቡብ ሱዳንና በጅቡቲ ከ 2.7 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ስደተኞች የሚሰጠውን የምግብና የገንዘብ ድጋፍ ከ 10 እስከ 30 በመቶ ለመቀነስ መገደዱን አስታውቋል፡፡

በሚመጡት ወራት ተጨማሪ ገንዘብ በወቅቱ ካለገኘም ድጋፉን ለማቋረጥ እንደሚገደድ ጨምሮ አስታውቋል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የምሥራቅ አፍሪካ ቀጠና ዳይሬክተር ሚካኤል ዱንፎርድ እንደተናገሩት “ስደተኞቹ በተለይ ለኮቪድ-19 መስፋፋት የተጋለጡ ናቸው። ምክንያቱም ደካማ ወይም በቂ ያልሆነ መጠለያ ፣ የጤና አገልግሎቶች፣ የንጹሕ መጠጥ ውኃና የንጽሕና አቅርቦት ያላቸው ናቸው፡፡"

ስደተኞቹ ዓለም አቀፍ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ባሳደረው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖም ሆነ በቫይረሱም እየተጠቁ መሆኑን መረጃው ጠቁሟል።

ዳይሬክተሩ አያይዘው ሴቶች፣ ሕፃናትና አዛውንቶች ለቫይረሱ የበለጠ ተጋላጭ በመሆናቸው በምግብ እጥረት በበሽታው የመጠቃት ዕድላቸውን ከፍ እንደሚያደርገው አመልክተዋል፡፡

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በተጣሉ ገደቦች በተፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ድቀት ምክንያት ብዙዎች ገንዘብ የማግኘት አጋጣሚን ማጣታቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም አመልክቷል፡፡

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በቀጣዮቹ ስድስት ወራት በቀጠናው የሚገኙትን ስደተኞች ለመደገፍ 323 ሚሊዮን ዶላር የጠየቀ ሲሆን ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የ22 በመቶ ብልጫ እንዳለውም አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም