በአዲስ አበባ በአጭር ጊዜ የተገነቡ የቱሪስት መዳረሻዎች እንደሰርቶ ማሳያ የሚወሰዱ ናቸው - የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ በአጭር ጊዜ የተገነቡ የቱሪስት መዳረሻዎች እንደሰርቶ ማሳያ የሚወሰዱ ናቸው - የፕሮጀክቱ አስተባባሪዎች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ በአጭር ጊዜ የተገነቡ የቱሪስት መዳረሻዎች እንደሰርቶ ማሳያ የሚወሰዱ ፕሮጀክቶች ናቸው ሲሉ የፕሮጀክቶቹ አስተባባሪዎች ተናገሩ።
ፕሮጀክቶቹ ዓለም አቀፋዊ መዳረሻ እንዲሆኑ ታስበው የተሰሩ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚዘጋጀው አዲስ ወግ የውይይት መድረክ ዛሬ 'ከሸገር ወደ አገር' በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የአንድነት፣ የእንጦጦ እና የወዳጅነት ፓርኮችን ግንባታ ሲያስተባበሩ የነበሩ አካላትና ሌሎች ባለጉዳዮችም ተገኝተዋል።
የእንጦጦ ተራራና ጫካ ወደ ፓርክነት በመቀየሩ በፓርኩ ውስጥ ሰፋፊ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ከጀመሩ ባለሀብቶች መካከል የኩሪፍቱ ሪዞርት ባለቤት አቶ ታዲዮስ በለጠ አንዱ ናቸው።
ሪዞርቱ በእንጦጦ ፓርክ ውስጥ ምግብ ቤት፣ መኝታ ክፍሎችና ሌሎች መዝናኛዎችን ያካተቱ የግንባታ ፕሮጀክቶችን እያካሄደ ይገኛል።
ባለቤቱ አቶ ታዲዮስ እንዳሉት እስካሁን በርካታ ሚሊዮን ብሮችን በቱሪዝም ዘርፍ ቢያውሉም የድካማቸውን ያህል ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ይናገራሉ።
በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የተገነቡት እነዚህ የመዝናኛ ፓርኮች ''ልፋትና ድካማችን ፍሬ እንዲያፈራ የሚያደርጉ ናቸው'' ሲሉ ተስፋቸውን ይገልጻሉ።
ሦስቱን ፕሮጀክቶች ሲያስተባብሩ ከቆዩት የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች መካከል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ እና የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ ሥራው አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት።
እነሱ እንደሚሉት የአንድነትና የወዳጅነት ፓርኮች የተገነቡበት ቦታ ለዘመናት የተጠራቀመ ቆሻሻ ለማስወገድ እንዲሁም ወንጀል መሥሪያና አስፈሪ ሥፍራ የነበረውን እንጦጦ ለማልማት ብዙ ተደክሟል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች እንደ አገር በዙሪያ ያለውን ሀብት ማየትና ማስተዋል የተጀመረባቸው እንደሆኑም ያስረዳሉ።
በቀጣይ ለሚሰሩ ሥራዎች ፕሮጀክቶቹ ሰርቶ ማሳያ መሆናቸውን ገልጸው፤ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ፣ በተወሰነ ጉልበትና ገንዘብ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ትምህርት የሰጡ መሆናቸውንም አስረድተዋል።
የሥራ ኃላፊዎቹ ፕሮጀክቶቹ እንደ አገር ጀምሮ መጨረስ እንደሚቻል የሚያሳዩ፣ ትልቅ ቅንጅታዊ አሰራር የተተገበረባቸውና ከፍተኛ የአመራር ቁርጠኝነት የታየባቸው ናቸው።
"ፕሮጀክቶቹ የአገሪቷን የቱሪዝም ክፍለ ኢኮኖሚ በተሻለ መልኩ የሚያሳድጉ ናቸው" ያሉት ደግሞ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ ናቸው።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ የአገራት ልምድ የሚያሳው ቱሪዝም ትልቅ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚያስችል ዘርፍ መሆኑና ከሚፈጥረውም 50 በመቶው ዕድሜያቸው ከ25 ዓመት በታች ለሆኑ ወጣቶች ነው።
"ዘርፉ አሁን ያለውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመቅረፍ የኢትዮጵያን የንግድ ሚዛን ለማሻሻል ያለው ሚና የጎላ ነው" ብለዋል።
"ፕሮጀክቶቹ የተመደበላቸውን ውስን ሀብት በአግባቡ የተጠቀሙ ናቸው" ያሉት ዶክተር እዮብ፣ ባለፉት ዓመታት 102 ፕሮጀክቶች 42 ቢሊዬን ብር ተጨማሪ ወጪ ማስወጣታቸውን አስታውሰዋል።
የዞማ ቤተ ጥበብ ባለቤት ወይዘሮ መስከረም አሰግድ ደግሞ የአንድነትና የእንጦጦ ፓርክን በጥበብ ካስጌጡት ሙያተኞች መካከል ናቸው።
ፓርኮቹ ነባራዊ ሁኔታቸውን ሳይለቁ ለትውልድ እንዲተላለፉ አስፈላጊው ጥንቃቄ ሁሉ ተደርጎ ስለመሠራታቸው ምሥክርነታቸውን ሰጥተዋል።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በበኩላቸው ፕሮጀክቶቹ አስገራሚ የፕሮጀክት አስተዳደር እንደታየባቸው ይገልጻሉ።
ፕሮጀክቶቹ በአገሪቷ አዲስ ምዕራፍ መክፈታቸውን ጠቁመው “የተለየ የፕሮጀክት አመራርና አፈጻጸም ሥርዓት የተከተሉ ናቸው” ብለዋል።
በመሆኑም ይህን የፕሮጀክት አስተዳደር ልምድ በተሞክሮነት ወስዶ ማስፋትና ተቋማዊ በሆነ መልኩ ማስቀጠል ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል።
አቶ ኃይለማሪያም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚያጓጉዛቸው መንገደኞች መካከል 70 በመቶ የሚሆኑት ወደ ሌላ አገር የሚሻገሩ ናቸው።
“እነዚህ የቱሪስት መዳረሻ ፕሮጀክቶች መንገደኞቹ ሰዓታቸውን የሚያሳልፉበትና ለአገሪቷም ትልቅ ጥቅም የሚያስገኙ ናቸው” ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት ሌሎች ባለድርሻ አካላትም የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክትን በአገር ደረጃ ማስፋቱ የሚደገፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የመዝናኛ ሥፍራዎች ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጡ በአግባቡ እንዲታሰብበት ጠቁመው በቀጣይ ቱሪዝሙንም የማስተዋወቅ ሥራ እንዲጠናከር ጠይቀዋል።
በሸገር ማስዋብ የተገኘውን ልምድ ወደ አገር ለማስፋት በቀጣይ ዓመት ኮይሻ፣ ጎርጎራና ወንጪን ለማልማት መታቀዱ ይታወቃል።