ቀጥታ፡

ኮቪድ-19 በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የከፋ ጉዳት አድርሷል - ጥናት

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 21/2012(ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ላይ የከፋ ጉዳት ማድረሱን አንድ ጥናት አረጋገጠ።

ከዘርፉ ተቋማት አብዛኞቹ በወረርሽኙ ለሚደርስባቸው ችግር ቅድመ መከላከያና ከችግሩ ማገገሚያ ስትራቴጂዎች እንደሌሏቸውም ተገልጿል።

የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም የሆነው የሆቴልና ቱሪዝም ስራ ማሰልጠኛ ማዕከል ኮቪድ-19 በዘርፉ ያደረሰው ተፅዕኖና ቀጣይ አቅጣጫዎች በሚል ጉባዔ እያካሄደ ነው።

ማዕከሉ ጥናቱን ያካሄደው ያለመረጃ በዘርፉ የሚነገሩ መረጃዎችን ለማጥራት፣ ሁሉን አቀፍና በአገር አቀፍ ደረጃ የተጣራ መረጃ ለማድረስና ቀጣይ መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም ዘርፉን ከኮቪድ-19 ተፅዕኖ ለመታደግ ያለመ መሆኑን መድረኩን የከፈቱት ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ገልፀዋል።

ሁለት ወራት የፈጀው ጥናት በሁሉም የአገሪቷ ክልሎች በ20 ከተሞች በሚገኙ የሆቴልና ቱሪዝም መስኮች በክልል የሆቴልና ቱሪዝም ባለሙያዎች ትብብር መረጃዎችን በማሰባሰብ መካሄዱ ተገልጿል። 

በዚህ ውስጥ 300 ሆቴሎች፣ አስጎብኚዎች፣ ሠራተኞች፣ የባሕል ቤቶች፣ ሬስቶራንቶች፣ ማኅበራት፣ ሱቆችና መንግስታዊ ተቋማት ይገኙበታል። 

ጥናቱ በማዕከሉ ተመራማሪዎችና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አማካሪዎች በቅንጅት መካሄዱም ተጠቁሟል።

በውጤቱም ዘርፉ ከየትኛውም ዘርፍ በበለጠ በኢኮኖሚ አቅም፣ በቢዝነስና በሰው ኃይል ረገድ ተጎጂ መሆኑ ተመላክቷል። 

ለአብነትም በኢኮኖሚ ረገድ በሆቴሎች የመኝታ አገልግሎት እንግዶችን የመቀበል አቅም ከወረርሽኙ በኋላ ማለትም ካለፈው መጋቢት ጀምሮ ከአምና ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻፃር 58፣ በገቢ 66፣ በምግብና መጠጥ ሽያጭ ገቢ 63 በመቶ ቀንሷል ተብሏል። 

በሬስቶራንቶች 88 በመቶ፣ እንዲሁም በመዳረሻ ስፍራዎች ቱሪስት የመቀበል አቅምም 97 በመቶ ገቢያቸው ቀንሷል። 

በአሁናዊ የቢዝነስ አቋም ረገድም በርካታ ድርጅቶች ስራ ከማቆም እስከ ከፊል ስራ ላይ ይገኛሉ፤ ከነዚህም ውስጥ ሆቴሎች 53 በመቶ ቀንሰዋል፣ ሌሎቹ አገልግሎት መስጠት አቁመዋል።

የቱሪዝም መዳረሻዎች 69 በመቶ አገልግሎት ሲያቆሙ፤ ባህላዊና ዘመናዊ ሬስቶራንቶችም በቅደም ተከተላቸው 67 እና 87 በመቶ ቀንሰው ከፊል አገልግሎት እየሰጡ ነው። 

በሠራተኞች ቅነሳ ረገድ ሆቴሎች 25 በመቶ፣ ሬስቶራንቶች 22 በመቶ እና የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች 28 በመቶ ቀንሰዋል። 

በሆቴሎች አገልግሎት መቀነስ ሳቢያ ሠራተኞች ከደመወዛቸው ውጭ የሚያገኙት ተጓዳኝ ገቢም ቀንሷል። 

ይህም የዘርፉን ሠራተኞች ገቢ በማሳጣት ማኅበራዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ሲያስከትል፤ የመንግስት የገቢ ግብር ላይም ተጽዕኖ አሳድሯል።

የተቋማቱ የስራ ትስስር የተስተጓጎለበት፣ ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት ያልቻሉበትና በሰው ሀብት ልማት ላይም ጥላ ያጠላበት ወቅት መሆኑም በጥናቱ ተረጋግጧል።

ይህም ሆኖ በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች ለአብነትም ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችና የቱሪዝም ድርጅቶች የአደጋ ጊዜ ስራ አመራርና ከችግር መውጫ አማራጭ ስትራቴጂ መንደፍ አለመቻላቸው ነው የተገለጸው።

በመሆኑም በቀጣይ በኢኮኖሚ መስክ የብድር አቅርቦት፣ የወጪ ቅነሳና የፋይናንስ ድጋፍን የማጠናከር አስፈላጊነት ተጠቅሷል።

አሁናዊ የቢዝነስ እንቅስቃሴን ለመታደግም በገበያ ልማት በኩል ማበረታቻዎች፣ የዋጋ ማስተካከያዎች፣ የቴክኖሎጂ ልማት፣ የኢንዱስትሪ ትስስርና አዳዲስ መዳረሻዎችን የማስተዋወቅ አማራጮች እንዲተገበሩ ተጠይቋል። 

በከፊል አገልግሎት ላይ የሚገኙ ድርጅቶችን ለመታደግ የሠራተኛ ደህንነት፣ የአገልግሎት ማስተካከያዎች፣ የቴክኖሎጂ አግልግሎት አሰጣጥ ትግበራ፣ ምርትና አገልግሎትን ማሰባጠር እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።

የአሰሪና ሠራተኛ መድረኮችን መጨመር፣ ሁለገብ ክህሎት ያላቸውን ሠራተኞች መጠቀም፣ የስራ ሠዓት ማሻሻል፣ የመንግስት ድጋፍና ሌሎቸ አማራጮችን መተግበር ይገባልም ተብሏል።

የቢዝነስ ቀጣይነት፣ የመንግስታዊ ተቋማት መልሶ መዋቀር፣ የሕግ ማዕቀፍ መሻሻል፣ የቱሪዝም መዳረሻዎች ዕድሳት ላይም በትኩረት ሊሰራ ይገባል ሲል ጥናቱ አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም