ቀጥታ፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፈዋል ተብለው የተከሰሱ ከ500 በላይ አሽከርካሪዎች ተቀጡ

ደብረ ማርቆስ, ነሐሴ 21/2012(ኢዜአ) የኮሮና ቫይረስን ለመከላከለ የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌ ተላልፈዋል ተብለው የተከሰሱ ከ500 በላይ አሽከርካሪዎች በገንዘብ እና እስራት መቀጣታቸውን የምስራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ ገለጸ።

አሸከርካሪዎቹ  የተቀጡት ከሐምሌ መጀመሪያ እስከ ነሐሴ አጋማሽ 2012 ዓ.ም  ባሉት ጊዜያት ውስጥ ነው።

የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል የሆነው የመምሪያው የመንገድ ትራፊክ አደጋ መከላከል እና ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ጎበዜ ይርሳው ለኢዜአ እንደተናገሩት ከ480 በላይ አሽከርካሪዎችን ከ500 ብር እስከ 2ሺህ ብር ተቀጥተዋል።

ቀሪዎቹ አሽከርካሪዎች ደግሞ  በፍርድ ቤት ተከሰው እስከ  ስድስት ወራት የሚደርስ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ከተቀጡባቸው ጥፋቶች መካከል ተሳፋሪን በግማሽ ቀንሰው ባለመጫን፣ ተሳፋሪዎቻቸውና ረዳት ጭምር የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል አለማድረግ ይገኙበታል።

በቀጣይም ህግን በማያከብሩ አሽከርካሪዎች  ቁጥጥሩን በመቀጠል  እርምጃዎች እንደሚወሰድ አብራርተዋል።

በአካባቢው የሚነባስ አሽከርካሪው  ወጣት ይርዳው እንዳወቅ በሰጠው አስተያየት  በሽታውን ለመከላከል  ያወጣውን መምሪያ ማክበር ተገቢ በመሆኑ  ፖሊስ ቁጥጥሩ  አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብሏል።

በእሱ በኩል ጥንቃቄው ለራሴ እና ቤት ለሚገኙ ቤተሰቦቸ ጭምር መሆኑን በመረዳት ህጉን እንደሚያከበርና ሌሎችም እንዲያከብሩ የሚመክር መሆኑን ተናግረዋል።

አንዳንድ አሽከርካሪዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛቸውን በአጋጫቸው ከማድረግ ባለፈ በአግባቡ እንደማይጠቀሙ መታዘባቸውን የገለጹት ደግሞ  የደብረማርቆስ ከተማ    ነዋሪ ወይዘሮ ያልጋነሽ ይሁኔ ናቸው።

"አሽከርካሪዎች ግዴታቸውን እየተወጡ ባለመሆኑ መንግስት የጀመረውን ቁጥጥር ማስቀጠል አለበት" ብለዋል።

ቁጥጥሩ በአሽከርካሪዎች ላይ  ብቻ ሳይሆን በፑል፣  መጠጥ ቤቶች፣  ገበያ አዳራሾች እና ሌሎችም ህዝብ በብዛት በሚሰበሰብባቸው ስፍራዎቹ መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል።

ኮሮን  ለመከላከል እንደሀገር የተደነገገው አዋጅ ከወጣበት ወዲህ በዞኑ በአጠቃላይ ከ2ሺህ በላይ አሽከርካሪዎች እርምጃ እንደተወሰደባቸውም ከፖሊስ መምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም