ቀጥታ፡

በሳዑዲና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ችግር ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተሰራ ነው ...አምባሳደሮች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2012(ኢዜአ)በሳዑዲ ዓረቢያና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች በችግር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊያን ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ አገራቸው ለመመለስ ከሀገራቱ መንግስትና ከሬድኤት ድርጅቶች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።።

በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱልአዚዝ አህመድ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን በሀገሪቱ እንደሚገኙ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በመሆኑም በችግር ውስጥ የሚገኙትን ኢትዮጵያዊያን ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ከሳዑዲ መንግስት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ አምባሳደር አብዱልአዚዝ ገለጻ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ባለው የዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ180 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።

በቅርቡም መንግስት ያወጣውን የኮሮና ወረርሽኝ መመሪያ በማሟላት ዜጎችን ወደ አገራቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ኖሯቸው በስራ ላይ የነበሩ ዜጎች በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ስራቸው በመቀዛቀዙ ችግር ውስጥ መግባታቸውንም ያነሱት አምባሳደሩ፤ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከሳዑዲ የምግብ ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ኮሚኒቲና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር በየቤታቸው ምግብ እንዲደርሳቸው እየተደረገ ነው ብለዋል።

በተመሳሳይ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው በርካታ ኢትዮጵያዊያን እንደሚገኙ በአገሪቷ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሱሌማን ደደፎ ገልጸዋል።

የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸውን ዜጎች ወደ አገራቸው ለመመለስ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

አምባሳደር ሱሌማን በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ስራ የፈቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በመጠለያ እንደሚገኙም ነው የገለጹት።

በሕጋዊ መንገድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን መብት ለማስጠበቅ ከአገሪቷ መንግስት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዜጎች በሰው አገር የሚደርስባቸውን ችግር ለመቀነስ ሕጋዊ መንገድ ተከትለው ከአገር እንዲወጡም መክረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም