ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከኃይል ሽያጭ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21/2012 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት በተጠናቀቀው የ2012 በጀት ዓመት ከኃይል ሽያጭ ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታወቀ።

የኃይል ብክነትን በመቀነስ ከ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ማዳን እንደተቻለም ገልጿል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ሽፈራው ተሊላ የተቋሙን የ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙንና የ2013 የትኩረት አቅጣጫዎችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያልተማከለ አደረጃጀትና አሰራር መተግበር፣ ሥራዎችን በሦስተኛ ወገን ማሠራትና ተቋሙን በቴክኖሎጂ ማዘመን ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫዎች ነበሩ ብለዋል።

በዚሁ መሠረት በትኩረት አቅጣጫዎቹ ሥር የተቋሙን ገቢ ማሳደግ፣ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ማስፋፋት፣ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ማሻሻልና የደንበኛ እርካታን የማሳደግ ሥራዎችም ተከናውነዋል።

በበጀት ዓመቱ ከኃይል ሽያጭ 13 ነጥብ 75 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ታቅዶ 11 ነጥብ 06 ቢሊዮን ብር መገኘቱን ገልጸዋል።

የተሰበሰበው ገቢ የዕቅዱን 80 በመቶ ያሳካ መሆኑንም አክለዋል።

ከኃይል ሽያጩ በተጨማሪ ለኤሌክትሪክ መስመር ግንባታና ማስቀጠያ፣ ከአሮጌ ንብረት ሽያጭና ከልዩ ልዩ የገቢ መሰብሰቢያ አማራጮች ገቢ መሰብሰቡን አቶ ሽፈራው አስረድተዋል።

በአጠቃላይ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከሁሉም የገቢ ምንጮች ለማግኘት በዕቅድ ከተያዘው 25 ነጥብ 38 ቢሊዮን ብር 14 ነጥብ 97 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 59 በመቶ ማሳካትም ተችሏል።

በሌላ በኩል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተቋሙ ቴክኒካልና ሰው ሰራሽ የኃይል ብክነትን የመቀነስ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በትክክል የማይሰሩ፣ የታቀጠሉና የቆሙ ቆጣሪዎች በወቅቱ እንዲቀየሩ የማድረግና የኃይል ፍጆታ ሂሳብ እንዲከፍሉ ወደ ክፍያ ሥርዓት የማስገባት ሥራ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

ያልተፈቀደ የኃይል ጭነት የሚጠቀሙትን መቆጣጣጠርና ሌሎችም የኃይል ብክነት የሚያስከትሉ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት ተደርጓል ብለዋል።

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ከሁለት ሺህ በላይ ኪሎዋት ሀወር የኃይል ብክነት በመቀነስ ከ1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ ከብክነት ማዳን መቻሉን አቶ ሽፈራው ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ በኤሌክትሪክ ኃይል መሠረት ልማቶች ላይ የሚፈጸም ስርቆትና ዝርፊያ በአሳሳቢ ሁኔታ መጨመሩንም ተናግረዋል።

በተፈጸሙት ድርጊቶች በሚሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት እንዲባክን አድርገዋል ብለዋል።

ተቋሙ ከፀጥታ አካላትና ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት ለሕግ በማቅረብ እርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑንም ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማቶች በፀጥታ አካላት መጠበቃቸው እንዳለ ሆኖ ኅብረተሰቡም አስፈላጊውን ጥበቃና ጥቆማ በማድረግ ሀብቱን ከጉዳት ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል።

የኅብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ለማሟላት ያረጁ መስመሮችን የመጠገንና የማሻሻል ሥራዎች መሠራታቸውንና በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል የሥነ ምግባር ጥሰት ለፈጸሙ የተቋሙ ሠራተኞች የጽሑፍ ማስጠንቂያ፣ የደመወዝ ቅጣት፣  ከደረጃ ዝቅ የማድረግና ከሥራ የማሰናበት አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ጠቁመዋል።

በ2013 ዓ.ም ኢንዱስትሪዎች ላይ ትኩረት በማድረግ 50 ሺህ ስማርት ቆጣሪያዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት እንዲሁም አንድ ሚሊዮን ደንበኞችን በመጨመር የተገልጋዮችን ቁጥር ወደ 4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ከፍ ለማድረግ ታቅዷልም ብለዋል።

በዚህ በጀት ዓመት ከኃይል ሽያጭ 16 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማግኘትና ከተለያዩ የገቢ መሰብሰቢያ አማራጮችም 25 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱን ጠቁመዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የግብዓት አቅርቦት ችግሮች፣ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት ስርቆት፣ ብልሹ አሰራርና የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተቋሙ ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

በኢትዮጵያ የኤሌትሪክ ኃይል ሽፋን 44 በመቶ እንደሆነና የኃይል አቅርቦት ሽፋኑም 33 በመቶው ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ጋር ከተገናኙ መስመሮች፤ ቀሪው ከዋናው የኤሌክትሪክ መስመር ጋር ካልተገናኙ መስመሮች እንደሚገኝ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም