በሻምቡ ከተማ ለተቸገሩ ወገኖችና ጤና ተቋማት ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በሻምቡ ከተማ ለተቸገሩ ወገኖችና ጤና ተቋማት ድጋፍ ተደረገ
ነቀምቴ/ሰቆጣ፣ ነሐሴ 21/2012(ኢዜ) በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሻምቡ ከተማ በኮሮና ምክንያት ለተቸገሩ 1ሺህ ወገኖችና ለሁለት የጤና ተቋማት ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የምግብና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።
ድጋፉ የተደረገው በዓለም ባንክ የሚደገፈው የኦሮሚያ ክልል የከተሞች ተቋማዊና የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም መሆኑን የፕሮግራሞ አስተባባሪ አቶ አምሳሉ ደሣለኝ ገልጸዋል።
በፕሮግራሙ የምግብ ድጋፍ የተደረገላቸው 1ሺህ ወገኖች 379 ኩንታል ዱቄት እንደሆነ አመልክተዋል።
ለሻምቡ አጠቃላይ ሆስፒታልና ለሻምቡ ከተማ ጤና ጣቢያ ደግሞ 975 ሊትር ሳኒታይዘር፣ 8 ሺህ 686 የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።
የምግብና ቁሳቁስ ድጋፉ 1ሚሊዮን 144ሺህ ብር እንደሚገመት አቶ አምሳሉ አመልክተው፤ በምዕራብ ወለጋ ለግምቢ ከተማም ተመሳሳይ ድጋፍ መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
በፕሮግራሙ የምዕራብ ኦሮሚያ አስተባባሪ አቶ ዲንቁ ጊሎ በበኩላቸው ለደምቢ ዶሎ፣ በደሌ፣ መቱና አጋሮ ከተሞች በተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደረጀ ቶሌራ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ድጋፍ ከተደረገላቸው የሻምቡ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ይተዳደሩበት የነበረው የቀን ስራ በኮሮና ምክንያት በመገደቡ ሲቸገሩ መቆየታቸውንና አሁን የተደረገላቸው ድጋፍ ችግራቸውን ለማቃለል እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል "ሄልቬታስ ኢትዮጵያ" መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የኮሮና ቫይረስ መመርመሪያ መሳሪያ አጋዥ ቁሳቁሶችን በሰቆጣ ከተማ ለሚቋቋመው ማዕከል ድጋፍ አደረገ።
በድርጅቱ የሰቆጣ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ገብራት ኪዴ ቁሳቁሶቹ 350ሺህ ብር በሆነ ወጪ ገዝተው ለአካባቢው ኮሮና መከላከል ገብረኃይል ማስረከባቸውን ገልጸዋል።
በቀጣይም ቫይረሱን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ፀሐፊው አቶ ሞገስ መርካ በርክክቡ ስነ ስርዓት ወቅት ድጋፉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ለሚቋቋመው የመመርመሪያ ማዕከል አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል።