በዞኑ 10 ሺህ የገጠር ነዋሪዎች የሶላር ኢነርጂ ተጠቀሚ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ 10 ሺህ የገጠር ነዋሪዎች የሶላር ኢነርጂ ተጠቀሚ ሆኑ
ጎንደር ፣ ነሐሴ 21/ 2012 (ኢዜ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተጠናቀቀው በጀት አመት ከ10 ሺህ በላይ የገጠር ነዋሪዎች የሶላር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆናቸውን የዞኑ ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው የዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ቡድን መሪ አቶ ማሩ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት የሶላር ኢነርጂ ተጠቃሚ የሆኑት በዞኑ 15 ወረዳዎች የሚገኙ የገጠር ነዋሪዎች ናቸው።
ቴክኖሎጂው ከፀሐይ ብርሃን በሚገኝ ኃይል የሚሰራና በቀን ከአምስት እስከ ስምንት ሰዓት የቤት ውስጥ የመብራት አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ለሬዲዮና ለተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ቻርጅ ማድረጊያ የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል።
አንዱ የሶላር ኢነርጂ ቴክኖሎጂ በአማካኝ እስከ አራት ሺህ ብር ዋጋ ያለው መሆኑን የገለጹት ቡድን መሪው ለነዋሪዎቹ በቅድመ ክፍያና በአጭር ጊዜ ብድር መከፋፈሉን አመልክተዋል።
ቴክኖሎጂው የአካባቢ አየር ብክለትን ከማስቀረት በተጨማሪ በኩራዝ ጭስ የሚመጣ በሽታን ለመታደግ አማራጭ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንደ ቡድን መሪው ገለጻ በዞኑ በተያዘው በጀት አመት ከ14 ሺህ በላይ የገጠር ነዋሪዎችን የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።
በምሥራቅ በለሳ ወረዳ የአርባ ፀጓር ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ችሎት ቢያድግልኝ ለቤት ውስጥ መብራት የሚጠቀሙት የኩራዝ ጭስ ለዓይናቸው ጤና ጠንቅ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል።
በፀሐይ ኃይል የሚሰራውን ቴክኖሎጂ መጠቀም በመጀመራቸው ዓይናቸው ላይ ይደርስ የነበረው ሕመም መቅረቱን ተናግረዋል።
"ወጪ የሌለው በመሆኑም ያለሥጋት እየተጠቀምኩበት ነው" ብለዋል።
ቴክኖሎጂውን ለቤት ውስጥ መብራት፣ ራዲዮ ለማድመጥና የሞባይል ስልክ ባትሪ ለመሙላት እየተጠቀምኩበት ነው" ያሉት ደግሞ በታች አርማጭሆ ወረዳ የሳንጃ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቢሰጥ ንጉሤ ናቸው።