የወረርሽኙን ስርጭት ለመቀነስ የይቅርታና የአመክሮ መስፈርት የሚያሟሉ የሕግ ታራሚዎች 'ቢለቀቁ' የሚል ምክረ ሀሳብ ቀረበ

184

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 21/2012(ኢዜአ) የይቅርታና የአመክሮ መስፈርት የሚያሟሉ የሕግ ታራሚዎች ቢለቀቁ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመቀነስ እንደሚረዳ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻፀም መርማሪ ቦርድ አስታወቀ።

መርማሪ ቦርዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀነ-ገደብ ሲጠናቀቅ ሊከሰቱ እንደሚችሉ ያሰጉትንና ትኩረት እንዲሰጣቸው በለያቸው የኮሮናቫይረስ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ምክረ ሀሳቦችን አቅርቧል።

ምክረሀሳቦቹን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈጻሚ አካላት ማቅረቡንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ቦርዱ ከነሐሴ መጨረሻ እስከ መስከረም 2013 ዓ.ም ማገባደጃ በርካታ ሰዎችን የሚያሰባስቡ ብሔራዊና ባሕላዊ ክብረ በዓላት ለኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምክንያት ስለሚሆኑ ጥንቃቄ እንደሚያሻ አሳስቧል።


የአሸንዳ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬና ሶለል፤ የዘመን መለወጫ፣ የመስቀል ደመራ፣ መውሊድና ሌሎች በዓላትን በመጥቀስ ከቫይረሱ ባሕሪይ አንጻር ሕብረተሰቡ አካላዊ ርቀቱን መጠበቅ እንዳለበት አመልክቷል።

በድጋፍም ይሁን በተቃውሞ፣ ታቅደውም ይሁን በድንገት የሚካሄዱ ሰልፎችና ስብሰባዎች በግንዛቤ ሥራና ሕግ በማስከበር ታግዘው መከናወን እንዳለባቸውም ጠቁሟል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሃይማኖት ሥርዓቶች፣ የገበያ፣ የሠርግ፣ የለቅሶ፣ የመዝናኛና ሌሎች ኩነቶች ለቫይረሱ መስፋፋት የሚኖራቸው ድርሻ ሰፊ በመሆኑ ከሃይማኖት መሪዎችና ከኀብረተሰብ አደረጃጀቶች ጋር ምክክር ማድረግ ይገባልም ብሏል።


የይቅርታና የአመክሮ መስፈርት የሚያሟሉ የሕግ ታራሚዎች ቢለቀቁ በማረሚያ ቤቶች የሚስተዋለውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመቀነስ እንደሚረዳም ቦርዱ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል።

የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት የማስተማርና ግንዛቤ የመፍጠር ሚና ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አስገንዝቧል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈጻሚነት ሲያበቃ አዋጁን ተክተው መንግስት የሚያደርገውን የመከላከል እንቅስቃሴ የሚደግፉ ሕጋዊ አሠራሮች አስቀድመው ካልታዩ ለኮሮናቫይረስ የሚያጋልጡ ሁኔታዎችን በሕግ ለመቆጣጠር ክፍተት ሊፈጠር እንደሚችል ነው መርማሪ ቦርዱ የገለጸው።

በሥራ ላይ ያሉትን ሕጋዊ አማራጮች በግልጽ ማወቅና ማሳወቅ እንዳለ ሆኖ አዳዲስና አጋዥ የሕግ ማዕቀፎች ሊታሰቡ እንደሚገባም ጠቅሷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርዱ ኃላፊነት በተያዘው ወር መጨረሻ እንደሚያበቃ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

መርማሪ ቦርዱ በሚያዚያ 2012 ዓ.ም ተቋቋሞ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።

ቦርዱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ዝርዝር አፈጻፀም ደንብና አተገባበሩን በመከታተል፣ በመቆጣጠርና እንደ አስፈላጊነቱ የማስተካከያ ሃሳቦችን ለባለድርሻ አካላት በማቅረብ ተፈፃሚ እንዲሆን የማድረግ ሃላፊነት የተሰጠው ነው።

በተጨማሪም የአዋጁን ዝርዝር አፈፃፀም ደንብ ከሕገ መንግስቱ አንፃር ክልከላ የተደረገባቸውን መብቶች ተገቢነታቸውን በጥልቅ በመመርመር ተፈፃሚነታቸውን ይከታተላል።

መንግስት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን መከላከልና መቆጣጠርን ዓላማ ያደረገ ለአምስት ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚያዚያ 2012 ዓ.ም ማወጁ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም