"ችግር ያልፈተነው ወዳጅነት" - ኢዜአ አማርኛ
"ችግር ያልፈተነው ወዳጅነት"
ኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ከመጋራታቸው በላይ ህዝቦቻቸው ዘመናትን የተሻገረ የንግድና ባህል ትስስር አላቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ግንኙነቱ ከመንግስት ለመንግስት በተጨማሪ የህዝብ ለህዝብ ዲፕሎማሲም ታክሎበታል።
"ያንተ ቤት ሲንኳኳ ..." እንዲሉ አንደኛው ችግር ሲገጥመው ሌላኛው ደራሽ ጎረቤት ሆነው ዘመናትን አሳልፈዋል።
ኢትዮጵያ በእርስ በርስ ጦርነት በታመሰችባቸው ወቅት ሱዳን በችግር ውስጥ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን ዋነኛ መሸሸጊያ ሆና አገግላለች።
ሱዳናዊያን በሚገጥማቸው ማናቸውም አይነት እንቅፋቶች ኢትዮጵያ ፈጥና ደራሽ መሆኗን ደግሞ ከአንድ ዓመት በፊት በሱዳን የተከሰተው ፖለቲካዊ ቀውስ ጥሩ ማሳያ ነው።
ሱዳንን ለሶስት አስርት ዓመታት ያስተዳደሩት ኦማር ሀሰን አልበሽር በህዝባዊ አመጽ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ አገሪቷ ለከፋ ፖለቲካዊ ቀውስ እንዳትዳረግ ኢትዮጵያ አበክራ መስሯቷን ሱዳናውያን ብቻ ሳይሆን ዓለም መስክሮላታል።
ሽግግሩ ከመስመር ወጥቶ ሱዳናውያን ወደ ለየለት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያመሩ ኢትዮጵያ ከፍተኛውን ሚና ተጫውታላች።
በወቅቱ ለስልጣን ሲፎካከሩ የነበሩ የሱዳን ሲቪልና ወታደራዊ ሃይሎች ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ለማድረግ ስምምነት እንዲፈራረሙ ኢትዮጵያ የአሸማጋይነት ሚናዋን በብቃትና በስኬት ተወጥታለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት ካርቱም በመገኘት ስምመምነቱ ለሱዳናዊያን መጻኢ ጉዞ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሲሉ ደስታቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ታሪካዊ ክስተት አንድ ዓመት በኋላም ትናንት በሱዳን ይፋዊ ጉብኝት አድርገዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው፣ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢኒጂነር ስለሺ በቀለና የመከላከያ ሚኒስትር ቀናዓ ያደታ የተካተቱበት ልዑክ ካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ እና የአገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የሞቀ አቀባባል አድርገውላቸዋል።
ጉብኝቱም በዋናነት የሁለቱን አገሮች ግንኙት ማጠናከርን ዓላማው ያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ጋር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድቡን ጨምሮ በሌሎች የሁለትዮሸ ጉዳዮችን ዙሪያ ውጤታማ የሆነ ምክክር አድርገዋል።
ቀጠናዊ ሰላምና ልማትም የውይይታቸው አካል እንደነበረ ነው ሁለቱ መሪዎች ከውይይታቸው በኋላ በጋራ በሰጡት መግለጫ ያስታወቁት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በወቅቱ በሁለቱ አገሮች እየመሩ ያሉ የለውጥ መንግስታት ለቀጣናው ብርሃን ሆነው እንደሚያገለግሉም አውስተዋል።
በውይይታቸውም በሁለትዮሸና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ምክክር ማድረጋቸውን ነው የገለጹት።
በሚቀጥለው ወር ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ጠቅሰው፤ በቆይታቸውም የህዳሴ ግድቡን ሊጎበኙ እንደሚችሉም አመላክተዋል።
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በበኩላቸው ኢትዮጵያና ሱዳን በባህል፣ በታሪክና በጉርብትና እንዳይለያዩ ሆነው የተሳሰሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ሁለቱ አገሮች የሚያከናውኗቸው በጎ ተግባራት ቀጠናውን በማስተሳሰር ረገድ ሞተር ሆኖ እንደሚያገለግልም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የሱዳን የፖለቲካ ሃይሎች ታሪካዊውን ሰላማዊ የፖለቲካ ሽግግር ሰነድ በፈረሙበት አንደኛ ዓመት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ሱዳንን መጎብኘታቸው ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸውም ነው ያወሱት።
''የፖለቲካ ቀውሱ ከፍ ወዳለ ችግር እንዳይሸጋገር እርስዎና ኢትዮጵያን የወከሉ ልዑኮች ላበረከታችሁት አስተዋጽኦም ልባዊ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ።
''ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሱዳንና ግብጽም ትልቅ እድል ይዞ መጥቷል'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ግድቡን በሚለከት የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ጥሩ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር በተጨማሪ ከሀገሪቱ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አብደል ፈታ አል ቡራሃን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም የሁለትዮሽ ግንኙነቱ በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይ መክረዋል።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው እንደሚሉት፤ የኢትዮ-ሱዳን ግንኙነት በብዙ መልኩ ይገለጻል።
አሁን ላይ ሁለቱም አገሮች በሽግግር ላይ መሆናቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ ''ሂደቱ በራሱ በርካታ ጉዳዮችን በጋራ እንዲሰሩ እድል ፈጥሯል'' ይላሉ።
የሚከሰቱ ችግሮች ቢኖሩም እንኳ ሁለቱም አገሮች በወንድማማችነት መንፈስ ተቀራርበው መፍታት እንደሚችሉም ነው ሚኒስትሩ የሚያስረዱት።
በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት የውጭ ቋንቋና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም በበኩላቸው ሁለቱ ጎረቤት አገሮች በሪፎርም ውስጥ መሆናቸውን ያነሳሉ።
በመሆኑም አገሮቹ በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ አጀንዳቸውን የጋራ አድረገው ለመስራት መስማማታቸውን ነው የተናገሩት።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት ይህን በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና መጫወቱን በማውሳት።
ሁለቱን አገሮች የሚያስተሳስረው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵዮያ ከሚያስገኘው ጥቅም ጎን ለጎን ለሱዳንም ፋይዳው የጎላ መሆኑን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ የሚናገሩት።
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በግድቡ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ ሱዳን መጠነኛ ቅሬታ ስታነሳ መቆየቷን አስታውሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከሱዳን መሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት "ግድቡን በሚመለከት የሚነሱ ቅሬታዎችን በውይይት ብቻ ለመፍታት ስምምነት ላይ ደርሰዋል" ብለዋል።
ጉብኝቱ ግድቡ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ለሱዳንም ጥቅም እንዳለውበማስረዳት ረገድ ትልቅ ስራ እንደተከናወነበት በመጥቀስ።
የግድቡ የሶስትዮሽ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት መከናወኑ ደግሞ "ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ" ማበጀት ረገድ አብነት የሚሆን ተግባር መሆኑንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይናገራሉ።
አፍሪካ መር የሆነው ድርድር በስኬት እንዲጠናቀቅ የሁለቱም አገሮች መሪዎች በቁርጠኝነት ለመስራት መተማመን ላይ ደርሰዋል።
ይህ ሂደት የስኬታማ ዲፕሎማሲ ማሳያ መሆኑን ነው ሚኒስትሩ ያብራሩት።
ቢልለኔ ስዩም በበኩላቸው መሪዎቹ ግድቡን ጨምሮ የትኛውንም አይነት ችግር በውይይት መፍታት በሚችሉበት ጉዳይ ላይ አጽንኦት ሰጥተው መወያየታቸውን ነው የሚገልጹት።
ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ሰላምና ልማት ከሱዳን ተነጥሎ ሊታይ እንደማይችል በኢትዮጵያ በኩል መገለጹንም ነው ሃለፊዋ ያብራሩት።
የሱዳን ፖለቲካዊ ሽግግር በሰላም እንዲፈታ ኢትዮጵያ ላበረከተችው አስተዋጽኦ ሱዳን ምስጋና ማቅረቧም ተገልጿል።
አሜሪካ "ሽብርተኝነትን ትረጃለሽ" በሚል ሱዳንን ካስቀመጠችበት 'ጥቁር መዝገብ' እንድታነሳት ኢትዮጵያ በብርቱ ሰርታለች።
''ሱዳን በዚህ መዝገብ ውስጥ መቀመጧ ደግሞ በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩ ይገለጻል።
ሱዳን ከዚህ መዝገብ ተነስታ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ድጋፍ እንድታገኝ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ጥረት እንደምትቀጥልም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ ይናገራሉ።
ኢትዮጵያንም ሆነ ሱዳንን የሚገጥማቸው ችግር የጋራ ጉዳት ማምጣቱ አይቀሬ በመሆኑ በማናቸውም ሁኔታ ተደጋግፈው ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋልም ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ናሱዳን በቀጣይነት በሁለትዮሸ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ለቀጠናው ትስስር እንደሚሰሩም ሚኒስትሩ ይፋ አድርገዋል።