ቀጥታ፡

በእነ ጃዋር መሐመድ ላይ የቀዳሚ ምርመራ ቀሪ ምስክሮችን ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ

አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 20/2012 ( ኢዜአ) ፍርድ ቤቱ በወንጀል ጉዳይ በተጠረጠሩት እነ ጃዋር መሐመድ ላይ የቀዳሚ ምርመራ ቀሪ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለነሐሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።

ፍርድ ቤቱ ለዛሬ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ቀጥሮ የነበረ ቢሆንም ከ4ኛ እስከ 9ኛ ድረስ ያሉ ተጠርጣሪዎች ባለመቅረባቸው ምስክርነት ሳይሰማ ቀርቷል።

ተጠርጣሪዎቹ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል።

በቀዳሚ ምርመራ መዝገብ ቁጥር 215585 አቶ ጃዋርን ጨምሮ 14 ተጠርጣሪዎች ያሉ ሲሆን በኮቪድ-19 ምክንያት ስድስት ተጠርጣሪዎች ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

ችሎቱ ባለፈው የተሰጠው ትዕዛዝ መፈጸሙን ለማረጋገጥ ግራ ቀኙን አዳምጧል።

1ኛ ተጠርጣሪ አቶ ጃዋር ከባለቤታቸውና ልጃቸው በቪዲዮ ኮንፈረንስ እንዲገናኙ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ አንድ ጊዜ መገናኘታቸውን ገልጸው፤ ቢያንስ በሳምንት ሁለት ጊዜ መገናኘት እንዲችሉ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል።

ከፖለቲካ ፓርቲያቸው ጋር እንዲገናኙና እንዲነጋገሩም ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

አራት ተጠርጣሪዎችም በፍርድ ቤት የኮቪድ-19 ምርመራ እንዲደረግላቸው የተሰጠው ትዕዛዝ አልተፈጸመም ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል።

ጠበቆች ባቀረቡት አቤቱታ የአቶ ጃዋርና አቶ በቀለ ገርባ ጓደኞችና የስራ ባልደረቦች እንዲጠይቋቸው በደብዳቤ ማመልከታቸውን ገልጸው፤ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል።

ከደንበኞቻቸው በሳምንት ሶስት ቀን እንዲገናኙ በተፈቀደው መሰረት እያገኟቸው ቢሆንም 'በቂ ጊዜ አልተሰጠንም' ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል።

የደንበኞቻቸው የባንክ አካውንት ባላወቁት መዝገብ መታገዱን የሚገልጽ ባለ አራት ገጽ አቤቱታም አቅርበዋል።

1ኛ ተጠርጣሪም የመጻፊያ መሳሪያ እንዲገባላቸው ጠይቀዋል።

12ኛ ተጠርጣሪ ሸምሰዲን ጠሃ በፖሊስ ድብደባ ደርሶባቸው ህክምና ማግኘታቸውን ገልጸው፤ ያገኙት ህክምና በቂ አይደለም በማለት የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ በተጠርጣሪዎችና በጠበቆች የሚቀርበው አቤቱታ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ ልክ መቅረብ እንዳለበት አስገንዝቧል።

አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ የምትገኝ በመሆኑ የፍርድ ቤቱም ትዕዛዝ ይህንን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት ገልጿል።

የባንክ አካውንት ታግዷል በሚል የቀረበው አቤቱታ የታገደበት መዝገብ በሚታይበት ፍርድ ቤት መሆን እንዳለበትም በማስረዳት፤ የታገደበትን መዝገብ ከዐቃቤ ሕግ ማወቅ እንደሚችሉ አስረድቷል።

ፖሊስ በበኩሉ ለሁሉም ተጠርጣሪዎች የኮቪድ-19 ምርመራ መደረጉን ለችሎቱ አስረድቷል።

12ኛ ተጠርጣሪ አሁን ባሉበት ማረፊያ ምንም አይነት ድብደባ እንዳልደረሰባቸው የገለጸው ፖሊስ፤ ህክምና እንዲያገኙ ማድረጉን በመግለጽ ተጨማሪ ህክምና ከፈለጉ እንደሚያሳክማቸው ገልጿል።

ዐቃቤ ሕግ ያቀረባቸው ምስክሮች በኮቪድ-19 ተይዘው ያልቀረቡት ከ4ኛ እስከ 9ኛ ድረስ ባሉት ስድስት ተጠርጣሪዎች ላይ የሚመሰክሩ በመሆኑ ተጠርጣሪዎቹ ከኮቪድ-19 ነጻ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የተደረገው ምርመራ ውጤት እስኪደረስ ድረስ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጥ ጠይቋል።

ግራ ቀኙን ያደመጠው ችሎቱ በቀረቡ አቤቱታዎች ላይ ትዕዛዝ ለመስጠትና ቀሪ የቀዳሚ ምርመራ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮችን ለመስማት ለነሐሴ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በዕለቱም ፖሊስ ሁሉም ተጠርጣሪዎች የኮቪድ-19 ምርመራ እንዲደረግላቸው ፍርድ ቤቱ የሰጠውን ትዕዛዝ ያልፈጸመበትን ምክንያት ቀርቦ እንዲያስረዳ አዟል።

የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከ4ኛ እስከ 9ኛ ድረስ ያሉ ተጠርጣሪዎችን የምርመራ ውጤት እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የባንክ አካውንትን መታገድ በተመለከተ ከዚህ ቀደም ትዕዛዝ መስጠቱንም አስታውሷል።

በችሎቱ ይህ ትዕዛዝ ከተሰጠ በኋላ ተጠርጣሪዎችና ጠበቆቻቸው የተለያዩ ሃሳቦችን አንስተዋል።

በተለይም በሌላ መዝገብ ዋስትና የተፈቀደላቸው ሰዎች በዋስ ሊወጡ እንዳልቻሉ በመግለጽ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እየተከበረ አይደለም ሲሉ ገልጸዋል። ዐቃቤ ሕግ የሚያቀርባቸው ማስረጃዎች እውነተኛ እንዳልሆኑም ተናግረዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ የሚሰጠው በያዘው መዝገብ ብቻ እንደሆነ አስረድቷል።

የፖለቲካ ዲስኩር የሚመስል ነገር በጠበቆች በኩል እንዳይቀርብም ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቆ፤ በችሎቱ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያለው ነገር ብቻ እንዲቀርብ ጠይቋል።

የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ካልተፈጸመም አቤቱታ መቅረብ ያለበት ትዕዛዙን ለሰጠው ፍርድ ቤት መሆን እንደሚገባውም በመግለጽ በአግባቡ አቤቱታ እንዲቀርብ ጠይቋል።

የሚቀርቡት አቤቱታዎች የቀዳሚ ምርመራ ባህሪን ካለመረዳት መሆኑን በመግለጽ፤ አቤቱታዎች በሚገባቸው ቦታዎች እንዲቀርቡ ጠበቆች ለደንበኞቻቸው እንዲያስረዱ እንዲደረግ አስገንዝቧል።

ምስክርን በተመለከተ የቀረበው አቤቱታ የህግ ስርዓቱን ተከትሎ መቅረብ እንደሚገባው ችሎቱ አስረድቷል።

የቀዳሚ ምርመራ የሚሰማው ተጠርጣሪዎችን ጥፋተኛ ወይም ነጻ ለማለት ሳይሆን የዐቃቤ ሕግ ማስረጃን ለማቆየት መሆኑን ገልጿል።

ትዕዛዝ ካልተፈጸመም በመዝገቡ ቀርቦ የሚታይ በመሆኑ አቤቱታው በዚያ መንገድ መቅረብ እንዳለበት አስረድቷል።

ጠበቆችም ለደንበኞቻቸው የችሎትን ስልጣን ማስረዳት እንደሚገባቸው አስገንዝቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም