ቀጥታ፡

ወለጋ ዩኒቨርሲቲ የመፃሕፍት ድጋፍ አደረገ

ነቀምቴ ኢዜአ ነሐሴ 20 /2012 ወለጋ ዩኒቨርሲቲ ለምሥራቅ ፣ ምዕራብ እና ሆሮ ጉዱሩ የወለጋ ዞኖች የመፃሕፍት ድጋፍ አደረገ ፡፡

ኮሮናን ለመከላከል የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የተማሪ መጻህፍት ጥመርታን ለማሻሻል ክልል አቀፍ የመፃህፍት ማሰባሰብ ዘመቻ መጀመሩን ተከትሎ የወለጋ ዩኒቨርሲቲም ድጋፉን ያደረገው  በዙሪያው ለሚገኙ ዞኖች ነው።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ሐሰን ዩሱፍ እንደገለጹት፤ ድጋፉ  ለማጣቀሻነት የሚያገለግሉ ግምታቸው 3 ሚሊዮን ብር የሆኑ  15 ሺህ የተለያዩ መፃሕፍት ናቸው።

መፃሕፍቱ በዞኖቹ ለተመረጡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከፋፍለው  የተማሪዎችን ችሎታ በማሳደግ ለዩኒቨርሲቲ ትምህርት እንዲዘጋጁ የሚያግዙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው  ወደፊትም ተመሳሳይ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው ብለዋል።

የምሥራቅ ወለጋ ዞን ትምህርት ቤቶች ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ደግፈ ባይሣ  ዩኒቨርሲቲው ያበረከታቸው የማጣቀሻ መፃሀፍት  የተማሪዎቻቸውና መምህራንን ችሎታ ለማሳደግ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደረጀ አበራም ዩኒቨርሲቲው ላደረገው ድጋፍ አመስግነው፤  መጪውን የትምህርት ዘመን  ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራ እንዲኖር  ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።፡

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ  በ2013 የትምህርት ዘመን  በነቀምቴ ከተማ  ልዩ ችሎታ ያላቸው ተማሪዎች የሚማሩበት አዳሪ ትምህርት ቤት በራሱ ወጪ ለመገንባት በቅርቡ የመሠረተ ድንጋይ ማስቀመጡ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም