የቤተ መንግስት አስተዳደር ሰራተኞች ለ‘‘ገበታ ለሀገር ” ፕሮጀክት የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለገሱ - ኢዜአ አማርኛ
የቤተ መንግስት አስተዳደር ሰራተኞች ለ‘‘ገበታ ለሀገር ” ፕሮጀክት የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለገሱ
አዲስ አበባ ነሐሴ 20/2012 (ኢዜአ) የቤተ መንግሥት አስተዳደር ሠራተኞች በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አነሳሽነት የተጀመረውን ‘‘ገበታ ለሀገር ” መርሐ ግብር ለመደገፍ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለገሱ።
በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የቤተ መንግስት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈሪ ፍቅሬ እንደገለጹት፤
ሠራተኞቹ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ እንዲውል ወስነዋል።
ሠራተኞቹ ውሳኔው ላይ የደረሱት በአገሪቱ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ፍሬአማ ሆነው በማየታቸው ነው ብለዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ውሃ ሙሌት ፣ የአንድነት ፓርክ ፣ የሸገር ወንዘች ዳርቻ ልማት እና የእንጦጦ ፓርክ አፈጻጸምን ለአብነት አንስተዋል።
”ገበታ ለሀገር” በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተጠነሰሰና ከአዲስ አበባ ውጭ ሶስት ቦታዎችን በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተዘጋጀ የገንዘብ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ነው።
ፕሮጀክቱበአማራ ክልል ጎርጎራ፣ በኦሮሚያ ክልል ወንጪና በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ኮይሻ አካባቢን በማልማት የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ያለመ ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን ጨምሮ የመስሪያ ቤቶች አመራሮችና ሠራተኞች ፕሮጀክቱን በመደገፍ አስተዋጽኦ ለማድረግ ቃል መግባት መጀመራቸወ ታውቋል።