የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ልዩ ተሰጥኦ ላላቸው ታዳጊ ስፖርተኞች ስልጠና ለመስጠት ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ

93
አዲስ አበባ ሰኔ 5/2010 ልዩ ተሰጥኦ ላላቸው ታዳጊ ስፖርተኞች በተለያዩ የስፖርት ማዕከላት ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል ቅድም ዝግጅት ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ። በቢሮው የውድድርና ተሳትፎ  ዳይሬክተር አቶ በኃይሉ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በ12 የስፖርት ዓይነቶች የሚሰጠው ስልጠና ከመጪው ዓመት ጀምሮ ይከናወናል። አትሌቲክስ፣ ቅርጫት ኳስ፣ ብስክሌት፣ ባድሜቴን፣ ክብደት ማንሳት፣ እጅ ኳስና  እግር ኳስ ስልጠናው ከሚሰጥባቸው የስፖርት አይነቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ። ስልጠናው በአራት ኪሎ ትምህርትና ስልጠና ተቋም፣ በራስ ሀይሉ ጅምናዚየም፣ በጃንሜዳ፣ በእጦጦ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና እና ትግል በነጻነት ቦታዎች እንደሚሰጥ አቶ በኃይሉ ገልጸዋል። በተለይም በአገሪቱ በእግር ኳስ ውስጥ የሚታየውን የግብ ጠባቂዎች ችግር ለመፍታት በሁለቱም ፆታዎች በእጦጦ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ሰፋ ያለ ስልጠና ለመስጠት የሚያስችል ቅድም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። ከግብ ጠባቂዎች ስልጠና ከሚካፈሉ ታዳጊዎች በቀር በዚህ ስልጠና የሚካፈሉ ስፖርተኞች ምልመላም ከሰኔ 9 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2010 ዓ ም በተካሄደው ከተማ አቀፍ የታዳጊ ወጣቶች የምዘና ውድድር ላይ ምልመላ መካሄዱን ነው የተናገሩት። በግብ ጠባቂዎች ስልጠና የሚካፈሉ ታዳጊዎች ምልመላ ደግሞ በመጪው ዓመት መጀመሪያ ወራቶች ላይ እንደሚካሄድ አመልክተዋል። በዚህ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ስፖርተኞች ስልጠና የሚካፈሉት ታዳጊዎች ቁጥራቸው 200 ያህል እንደሆኑና እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች እንደሆኑ የተገለጸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም