ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በሱዳን ቆይታቸው የተሳካ ዲፕሎማሲያዊ ስራ አከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በሱዳን ቆይታቸው የተሳካ ዲፕሎማሲያዊ ስራ አከናውነዋል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 20/2012(ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ በሱዳን በነበራቸው የስራ ጉብኝት ህዳሴ ግድብን ጨምሮ በሌሎች የሁለትዮሸ ጉዳዮች ላይ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወናቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሱዳን የነበራቸውን የአንድ ቀን የስራ ጉብኝት አጠናቀው ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል።
በነበራቸው ቆይታም ከሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክና ከሽግግር መንግስቱ ሉአላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አብደል ፈታ አል ቡርሃን ጋር ተወያይተዋል።
ውይይታቸውም በዋናነት ህዳሴ ግድብን በተመለከተና በሌሎች ሁለትዮሽ እንዲሁም ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የመልማት መብቷን ሱዳን እንደምታከብርና በግድቡ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች በድርድር ብቻ መፈታት እንዳለባቸው መናገራቸው ይታወሳል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ጉብኝቱን አስመልክቶ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያና ሱዳን ሽግግር ላይ መሆናቸው ይበልጥ ተቀራርበው እንዲሰሩ እድል ፈጥሯል።
የኢትዮጵያና ሱዳን ወዳጅነት ከመሪዎች ባሻገር ህዝባዊ መሰረት እንዳለውም ጠቅሰዋል።
ከዚህ አንጻር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሱዳን ቆይታቸው የኢትዮ-ሱዳን ግንኙነትን ይበልጥ ማስተሳሳር በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ከሱዳን መሪዎች ጋር መምከራቸውንም ገልጸዋል።
ሱዳን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ መጠነኛ ቅሬታ ስታነሳ መቆየቷን አስታውሰው፤ "መሪዎቹ ግድቡን በሚመለከት የሚነሱ ቅሬታዎችን በውይይት ብቻ ለመፍታት ስምምነት ላይ ደርሰዋል" ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ግድቡ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ለሱዳንም ጥቅም እንዳለው ማስረዳታቸውን አቶ ገዱ አውስተዋለ።
የሶስትዮሽ ድርድሩ በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት መከናወኑ ደግሞ "ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ" ማበጀት እንደሚገባ አመላካች መሆኑን መሪዎቹ ማንሳታቸውን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።
በመሆኑም አፍሪካ መር የሆነው ድርድር በስኬት እንዲጠናቀቅ የሁለቱም አገሮች መሪዎች በቁርጠኝነት ለመስራት መተማማን ላይ መድረሳቸውንም ጠቁመዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ አሜሪካ "ሽብርተኝነትን ትረጃለሽ" በሚል ሱዳንን ካስቀመጠችበት 'ጥቁር መዝገብ' እንድታነሳት በብርቱ መስራታቸውንም አንስተዋል።
''ሱዳን በዚህ መዝገብ ውስጥ መቀመጧ ደግሞ በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል'' ብለዋል።
በመሆኑም መሪዎቹ በውይይታቸው "ኢትዮጵያንም ሆነ ሱዳንን የሚገጥማቸው ችግር የጋራ ጉዳት ማምጣቱ አይቀሬ መሆኑን በመግለጽ በማናቸውም ሁኔታ ተደጋግፈው ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል" ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት የውጭ ቋንቋና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም መሪዎቹ የትኛውንም አይነት ችግር በውይይት መፍታት በሚችሉበት ጉዳይ ላይ አጽንኦት ሰጥተው መወያየታቸውን ተናግረዋል።
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ የሱዳን ፖለቲካዊ ሽግግር በሰላም እንዲፈታ ኢትዮጵያ ላበረከተችው አስተዋጽኦ ምስጋና ማቅረባቸውንም ሃላፊዋ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት ከሱዳን ተነጥሎ ሊታይ እንደማይችል ማንሳታቸውንም ነው የተናገሩት።
መሪዎቹ የሁለቱ አገሮች ስኬት ከቀጠናው ባለፈ ለአፍሪካ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በማመን ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናከር በቁርጠኝነት ለመስራት መተማመናቸውንም ሃላፊዋ ጠቁመዋል።
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በቅርቡ ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ የተገለጸ ሲሆን፤ በቆይታቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።