ፋውንዴሽኑ ለችግር ለተጋለጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
ፋውንዴሽኑ ለችግር ለተጋለጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 19/2012(ኢዜአ) ዲቦራ ፋውንዴሽን የኮሮና ቫይረስ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ ለችግር ለተጋለጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች የአልባሳትና የምግብ ግብዓት ድጋፍ አደረገ።
ፋውንዴሽኑ ድጋፍ ያደረገው ወርልድዋይድ ኦርፋን ፋውንዴሽን ለሚደግፋቸው ሕፃናት፣ እናቶችና የኤች.አይ.ቪ/ቫይረስ ላለባቸው ከ160 የሚልቁ ሰዎች ነው።
በአቶ አባዱላ ገመዳና ቤተሰቦቻቸው የተመሰረተው ዲቦራ ፋውንዴሽን የበጎ አድራጎት ድርጅት የሕፃናት መብቶች፣ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ዜጎች መብትና ጥቅም የማስከበርና ማኅበራዊ ልማትን ዓላማ አድርጎ መቋቋሙን የፋውንዴሽኑ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰይፉ ገብረማርያም ገልጸዋል።
ከተቋቋመ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ፋውንዴሽኑ የኮቪድ-19ን መከሰት ተከትሎ ለአቅመ ደካሞች፣ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ልጆችና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ማኅበራት የምግብ ቁሳቁስ፣ የንፅህና መጠበቂያዎችና የአልባሳት ድጋፍ አድርጓል።
ዛሬ ያበረከተው 200 ሺህ ብር የሚገመት የምግብ ግብዓትና የአልባሳት ድጋፍ ቀጣይነት ያለው መሆኑንም አቶ ሰይፉ ተናግረዋል።
ድጋፉ ያለንን በማካፈል በችግር ላይ ያሉ ወገኖች ብቻቸውን እንዳልሆኑና አጋር እንዳላቸው እንዲረዱ የተደረገ ነው ብለዋል።
የወርልድዋይድ ኦርፋን ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ሶፊ መንግስቱ ዲቦራ ፋውንዴሽን ለሕፃናቱ የምግብና የትምህርት መሳሪያ ድጋፍ በማድረግ ሲያስተምርና ደጋፊ የሌላቸውን እናቶች ሲረዳ መቆየቱን ተናግረዋል።
በፋውንዴሽኑ በማኅበረሰቡ ውስጥ ደጋፊ እናት ተደርጎላቸው የሚኖሩ የኤች.አይ.ቪ/ቫይረስ ያለባቸው ልጆች መኖራቸውንም ገልጸዋል።
እናቶቹ በተለይ የዕለት ጉርሳቸውን ተሯሩጠው የሚያገኙ በመሆናቸው ላለፉት ወራት በፋውዴሽኑ የምግብ ድጋፍ ሲደረገ መቆየቱንና ልጆቹም ትምህርት እንዳይረሱ በቤታቸው በታላላቆቻቸው ድጋፍ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉን ጠቁመዋል።
ዲቦራ ፋውንዴሽን ላደረገው ድጋፍ አመስግነው በየወሩ ለተረጂዎች ድጋፍ ማድረግ ዘላቂ መፍትሄ አይሆንምና በመንግስትና በኀብረተሰቡ ትብብር ራሳቸውን የሚያስችላቸው ድጋፍ ያሻቸዋል ብለዋል።
ድጋፍ የተደረገላቸው እናቶችም ቀደም ሲል የልጆቻቸው ሙሉ ወጪ በፋውንዴሽኑ ተሸፍኖ ስለሚማሩ ኑሮን ለማሸነፍ የቀን ገቢ በሚያስገኙ ስራዎች ይሰማሩ እንደነበር ገልጸዋል።
በኮሮና ቫይረስ መከሰት ሳቢያ ቤት ለመዋል ቢገደዱም ፋውንዴሽኑ በሚያደርግላቸው ድጋፍ ኑራቸውን እየገፉ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የኮሮና ቫይረስ ጠፍቶ መልካም ጊዜ እስከሚመጣ ሁሉም የአቅሙን እንዲደግፋቸውም ጠይቀዋል።