ቀጥታ፡

የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና የደን ልማት ስራዎች ማዕቀፋዊ ድጋፍ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 19/2012(ኢዜአ) የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና የደን ልማት ለሚከናወኑ ስራዎች ማዕቀፋዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዑክ አባላት በህብረቱ የኢትዮጵያ ቢሮ ቅጥር ግቢ አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

የአየር ንብረት ለውጥና የደን ልማት ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት የትብብር መስኮች መካከል የሚጠቀስ መሆኑን የህብረቱ የኢትዮጵያ ልዑክ የዓለም አቀፍ እርዳታና ትብብር ኦፊሰር ፒዬር-ሉክ ቫንሀቨርቤክ ገልጸዋል።

በሁለቱ መስኮች ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት በአውሮፓ ህብረት የፋይናንስ ድጋፍ አማካኝነት እየተከናወነ መሆኑንና ይሄም ከአረንጓዴ አሻራ ጋር ትስስር እንዳለው አመልክተዋል።

ፕሮጀክቱ እ.አ.አ ከ2018 መገባደጃ አንስቶ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝና እ.አ.አ በ2021 የሚጠናቀቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ መዋቅር በአየር ንብረት ለውጥ ወደ ማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እንዲሸጋገር ለማስቻል ፕሮጀክቱ ዓላማ አድርጎ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የደን ጥበቃ ስራ፣ የመሬት አጠቃቀም ቁጥጥር ስርአት ማጠናከር፣ የደን አስተዳደር ስርአቱን ማዘመንና በደን ልማት ስራ ውስጥ የክትትልና ቁጥጥር አቅምን ማሳደግ በፕሮጀክቱ ውስጥ መካተታቸውን አመልክተዋል።

በአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተተከሉትን ችግኞች ተንከባክቦ እንዲጸድቅ ማድረግ ለዚህም አስፈላጊውን የክትትልና ቁጥጥር ስርአት መዘርጋት ዋናው ቁም ነገር ነው ብለዋል ፒዬር-ሉክ ቫንሀቨርቤክ።

የአውሮፓ ህብረት ከደን ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ መስኮች ውጪ በጤና፣ በትምህርት፣ በመሰረተ ልማትና በተመጣጠነ ምግብ ዙሪያ ለኢትዮጵያ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አክለዋል።

የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ በበኩላቸው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ (ሲአርጂኢ) የሀብት ድጋፍ የሚያደርግና የስትራቴጂውን ተግባራዊነት በጋራ የሚገመግም መድረክ እ.አ.አ በ2018 መቋቋሙን ገልጸዋል።

የጋራ መድረኩ የልማት አጋር የሆኑ አገሮችንና ዓለም አቀፍ ተቋማት የያዘ መሆኑን የዛሬው መርሃ ግብርም የመድረኩ አባላት ላለፉት ቀናት ሲያካሂዱት የነበረው የችግኝ ተከላ አካል እንደሆነ ተናግረዋል።

የአውሮፓ ህብረት የሲአርጂኢ መድረክ አባል እንደሆነና ህብረቱን ጨምሮ ሌሎች የመድረኩ አባላት ለኢትዮጵያ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነም ገልጸዋል።

ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ  እ.አ.አ እስከ 2030 የሚቆይ እንደሆነና የልማት አጋሮቹም ይሄን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አምስት ቢሊዮን ችግኝ መተከሉ የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ግንኙነታቸውን ማጠናከር አላማ ያደረገ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት እ.አ.አ በ2016 መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።

ኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት የአፍሪካና የዓለም አገሮች ዋንኛ የልማት አጋር ተብለው ከሚጠቀሱት ዋንኛዋ ስትሆን ህብረቱ እ.አ.አ ከ2014 እስከ 2020 ድረስ 815 ሚሊዮን ዩሮ የሚሆን ድጋፍ ለኢትዮጵያ ማድረጉን ከአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም