ጎንደርን ጨምሮ በዘጠኝ ከተሞች የተቋረጠባቸውን የኤሌትሪክ አገልገሎት ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጎንደርን ጨምሮ በዘጠኝ ከተሞች የተቋረጠባቸውን የኤሌትሪክ አገልገሎት ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ ነው
ጎንደር፣ ነሐሴ 19/2012(ኢዜአ) ጎንደርን ጨምሮ በተለያዩ ዘጠኝ ከተሞች ከትናንት ጀምሮ የተቋረጠባቸውን የኤሌትሪክ አገልገሎት ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት የጎንደር ዲስትሪክት አስታወቀ፡፡
የዲስትሪክቱ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ አበራ ለኢዜአ እንደተናገሩት ትናንት ከቀኑ አስር ሰዓት አካባቢ በጎንደር ከተማ ሐምሌ አምስት በሚባለው አውራ መንገድ አጠገብ ባለ 66 ኪሎ ቮልት የኤሌትሪክ ኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶ በሌቦች ተፈቶ ወድቋል።
ከወደቀው ምሰሶ ላይ የነበረ ብረት መዘረፉንም ተናግረዋል።
ድርጊቱ የተፈጸመው ከባህርዳር ወደ ጎንደር ከተማ በተዘረጋው ከፍተኛ የኤሌትሪክ ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ላይ እንደሆነ አመልክተዋል።
በዚህም ጎንደር ከተማ በከፊል፣ በማዕከላዊና ሰሜን ጎንደር ዞኖች የሚገኙ 8 ከተሞች ደግሞ ሙሉ በሙሉ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መቋረጡን አስታውቀዋል።
አገልግሎቱ ከተቋረጠባቸው ከተሞች መካከልም ደባት፣ ደባርቅ፣ አምባ ጊዮርጊስ፣ ጃናሞራ፣ አዲአርቃይ፣ ዛሪማ፣ ወቅንና ትክል ድንጋይ ይገኙበታል።
ዲስትሪክቱ ጉዳት የደረሰበትን ከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶ በጊዚያዊ የእንጨት ምሰሶዎች ለመተካት ባለሙያዎችን አሰማርቶ ርብብርብ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመብራት አገልግሎት ከተቋረጠባቸው ተቋማት አንዱ መሆኑን ጠቁመው፤ በአሁኑ ወቅት ከሌላ ማከፋፈያ ጣቢያ መስመር በመዘርጋት አገልግሎት እንዲያገኝ መደረጉን አመልክተዋል።፡
አገልግሎቱ የተቋረጠባቸው ከተሞች እስከ ነገ ጥዋት አገልግሎቱን ለማስቀጠል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ህብረተሰቡም ይህንን በመረዳት በትዕግስት እንዲጠባበቅ መልዕክታቸውን አስላልፈዋል።