ቀጥታ፡

ሱዳን የኢትዮጵያን በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብት ታከብራለች ... ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ

ካርቱም፣ ነሃሴ 19/2012(ኢዜ) ሱዳን የኢትዮጵያን በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብት እንደምታከብር የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተወያይተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የተመራ ልዑክ ለስራ ጉብኝት ነው ዛሬ ረፋዱ ላይ ካርቱም የገባው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካርቱም ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክን ጨምሮ የአገሪቱ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።

ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በውይይታቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚጠናከርበት ጉዳይ ላይ መክረዋል።

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢትዮጵያና ሱዳን ዘመናት የተሻገረ ወዳጅነት እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ግንኙነቱ ወደተሻለ ደረጃ ከፍ እንዲል እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን ሱዳን እንደምታከብር ጠቁመው፤ የህዳሴ ግድብን በሚመመለከት የሚነሱ ጉዳዮች በድርድርና ውይይት ብቻ መፈታት አለባቸው ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሱዳንም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል።

''በመሆኑም ግድቡ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የሱዳንም ጭምር ነው'' ብለዋል።

በኢትዮጵያና ሱዳን መካከል በድንበርና በሌሎችም መስኮች የሚነሱ ጉዳዮች በሁለትዮሽ ውይይት እንደሚፈቱም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሮቹ የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም