ቀጥታ፡

አበዳሪ ሀገራት የዕዳ ስረዛና የክፍያ ጊዜ እንዲያራዝሙ የማግባበት ሥራ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የብድር ስረዛ እንዲደረግላትና ዕዳ የመክፈያ ጊዜ እንዲራዘምላት አበዳሪ ሀገራትን የማግባባት ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን አምባሳደሮች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በታዳጊ አገሮች የሚያስከትለውን የምጣኔ ሀብት ጫና ለመቋቋም የቡድን 20 አባል አገሮች የዕዳ ስረዛ እንዲያደርጉና የመክፈያ ጊዜ እንዲያራዝሙ ጥሪ አቅርበው ነበር።

ይህንን ተከትሎ በተለያዩ ሀገራት የተወከሉ ኢትዮጵያዊያን አምባሳደሮች የዕዳ ስረዛ እንዲደረግ በተወከሉበት አገር ድርድር እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ለኢዜአ እንዳሉት ቻይና ከአፍሪካ ጋር ባላት የትብብር ፎረም በዕዳ ስረዛ ላይ ውይይቶች ተደርገዋል።

"የቡድን 20 አባል አገሮች ለታዳጊ ሀገሮች የዕዳ መክፈያ ጊዜ እስከ 2020 መጨረሻ ማራዘማቸውን ተከትሎ ተፈጻሚነቱ ላይ ከቻይና መንግሥት ጋር ውይይት እየተደረገ ነው" ብለዋል።

ለዚህም ኢትዮጵያ ከቻይና ጋር ያላት የብድር ሥምምነት በሚታይበት ሁኔታ ላይ  ሀሳብ አቅርበው እየተመከረበት መሆኑን ገልጸዋል።

የቡድን 20 አባል አገሮች በመሪዎች ደረጃ ያደረጉትን ሥምምነት ተግባራዊ ለማድረግ በቻይና በኩል ዝግጁነት እንዳለም ተናግረዋል።

አፍሪካ በኮቪድ-19 ምክንያት ከሚያጋጥማት የምጣኔ ሀብት ችግር እንድትወጣ የዕዳ ቅነሳና ስረዛ እንዲሁም የብድር መክፈያ ጊዜን ከማራዘም ያለፈ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም አምባሳደር ተሾመ ጠቁመዋል።

በመሆኑም ምጣኔ ሀብቱን መልሶ ለማነቃቃት አዲስ ካፒታል ማግኘት በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ከቻይና ኩባንያዎችና ሌሎች አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ናቸው።

በጀርመን የኢትዮጵያ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሙሉ ሰለሞን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ የዕዳ ቅነሳ እንዲደረግ ከጀርመን መንግሥት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ለውጥ ለመደገፍ ከጀርመን መንግሥት በኩል ዝግጁነት እንዳለም አምባሳደር ሙሉ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል እያደረገች ያለውን ጥረት በተለያየ መንገድ ለመደገፍ አገራቱ ዝግጁ መሆናቸውን አምባሳደሮቹ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ያለባት አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ከ27 ቢሊዮን ዶላር በላይ መድረሱን አዲስ ዘመን ጋዜጣ በሚያዝያ ወር መዘገቡ ይታወሳል።

ከዚህ ውስጥ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሆኑት የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና ኢትዮ-ቴሌኮም ከቻይና መንግሥት ተበድረው ያልከፈሉት 4.5 ቢሊዮን ዶላር ዕዳ የመክፈያ ጊዜ መንግሥት ባደረገው ድርድር እንዲራዘም መደረጉ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም