ቀጥታ፡

በአፋር ክልል የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል በሄሊኮፕተር በመታገዝ እየተሰራ ነው

ሠመራ፣ ነሐሴ 19/2012 (ኢዜአ) በአፋር ክልል የለማ ሰብልና ግጦሽ መሬት ላይ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል በሄሊኮፕተር በመታገዝ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እርሻ፣ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ገለጸ።

የአንበጣ መንጋው በክልሉ 29 ወረዳዎች የተከሰተ በመሆኑ በመከላከሉ ሂደት የኅብረተሰቡ ንቁ ተሳትፎ እንደሚያስፈልግም ተመልክቷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ ዓሊ ሁሴን እንደገለጹት በክልሉ የአንበጣ መንጋ ክስተት በተደጋጋሚ እየተስተዋለ ነው።

በተለይም በቅርቡ ከሱማሌላንድ በኩል ገብቶ በክልሉ በ22 ወረዳዎች የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ከግብርና ሚኒስቴር ጋራ በመሆን ለመከላከል ጥረት መደረጉን አውስተዋል።

አሁን ደግሞ  ከየመን ከፍተኛ መጠን ያለው የአንበጣ መንጋ ወደ ክልሉ በመግባት በ29 ወረዳዎች  እንደተከሰተ አስታውቀዋል።

በዚህም   ከ58 ሺህ ሄክታር በላይ የለማ ሰብልና ግጦሽ መሬት ላይ የአንበጣ መንጋው መታየቱን ጠቅሰው ለመከላከል ክልሉ ከፌደራል መንግሥት ጋር በመተባበር በሄሊኮፕተርና ተሽከርካሪ  በመታገዝ  የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።

እስካሁን  ከ30 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የመከላከል ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።

ይህም ሆኖ አሁን  ያለው የአየር ንብረት ለአንበጣ መንጋው በቀላሉ መራባት ምቹ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሰብልና የእንስሳት ግጦች ሣር ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል በመንግሥት ብቻ ጥረት ሊሳካ እንደማይችል ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡም ይህንን በመረዳት  በመከላከሉ ሥራ ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የድርሻውን መወጣት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

በተለይም የአንበጣ መንጋው ያረፈበትን ቦታ በመጠቆምና ባህላዊ የመከላከል ዘዴዎችን በመጠቀም ለመከላከል በየደረጃው የሚገኘው አመራር ኅብረተሰቡን በማስተባባር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የአበአላ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ኑር በበኩላቸው በወረዳው በተለያየ ሰብል ከለማው 15 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ ባለፉት አራት ቀናት ከሦስት ሺህ በላይ ሄክታር በላይ በመንጋው ጉዳት እንደደረሰበት ተናግረዋል።

በተሽከርካሪና ሰው ኃይል በመታገዘ የመድኃኒት ርጭት በማካሄድ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በክልሉ በተያዘው የክረምት ወቅት ከ88 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በተለያየ የሰብል ዘር እየለማ ካለው መሬት 2 ሚሊዮን 300ሺህ ኩንታል ለማግኘት መታቀዱን ከእርሻ፣ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም