ቀጥታ፡

በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የሕዳሴ ግድብ ተሳትፎን አጠናክረው ቀጥለዋል

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 19/2012( ኢዜአ) በአሜሪካ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች በሕዳሴ ግድብ ላይ አገራቸው የያዘችውን ትክክለኛ አቋም የማስረዳት ተግባራቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለጹ።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍጹም አረጋ ለኢዜአ እንዳሉት የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ደረጃ ውሃ ሙሌት መጠናቀቅ በዳያስፖራው ዘንድ መነቃቃትን ፈጥሯል።

በግድቡ ላይ እየተካሄደ ባለው ድርድር ግብጽ የምታቀርበውን የተዛባ መረጃ ለማጥራትም በተለያዩ መንገዶች ተሳትፏቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በአሜሪካ ግብዣና በገንዘብ ሚኒስትሩ አስተባባሪነት አካሂደውት በነበረው ውይይት በአሜሪካ በኩል የግብጽን ሃሳብ የመደገፍ ሁኔታ እንደነበር አምባሳደር ፍጹም አውስተዋል።

በመሆኑም ዳያስፖራው አሜሪካዊያን ኢትዮጵያ ስለያዘችው ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ግልጽ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በተለያየ አደረጃጀት እየሰራ ነው ብለዋል።

ምሁራንም ስለ ግድቡ ትክክለኛውን መረጃ የሚያሳዩ ተከታታይ ጹህፎችን በማውጣት ተጽዕኖ ለመፍጠር የጀመሩትን ስራ ቀጥለዋል።

በተመሳሳይ ሌሎች የዳያስፖራ አባላት የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመጠቀምና በየአካባቢው የሚገኙ ተመራጮችም መረጃ እንዲደርሳቸው በማድረግ ስራዎችን መቀጠላቸውን ገልጸዋል።

ዳያስፖራው በሃሳብ ብቻ ሳይሆን በገንዘብም ድጋፍ ለማድረግ ያለው ተነሳሽነት ጨምሯል።

ቀደም ሲል የባንክ ሂሳብ ቁጥር ባለመከፈቱ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በቦንድ ግዥና በስጦታ የሚሳተፉበት ዕድል ዝቅተኛ እንደነበር አስታውሰዋል።

አሁን ዳያስፖራው በሚፈልገው መንገድ የገንዘብ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የባንክ ሲሳብ ቁጥር በመከፈቱ አማራጮችን በመጠቀም ድጋፍ ማድረግ እንደሚቻል አስታውቀዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌትን ተከትሎ በዳያስፖራው ዘንድ የተፈጠረውን መነቃቃትና አመኔታ ለማስቀጠል ይሰራልም ብለዋል አምባሳደር ፍጹም።

የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ዳያስፖራውን በማስተባበር የሃሳብና የገንዘብ ድጋፉን ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም