በአጋርፋ ወረዳ ለተፈናቀሉ ወገኖች 5 ሚሊዮን 900 ሺህ ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በአጋርፋ ወረዳ ለተፈናቀሉ ወገኖች 5 ሚሊዮን 900 ሺህ ብር የሚገመት ድጋፍ ተደረገ
ጎባ፣ ነሐሴ 19/2012 (ኢዜአ) በተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ኮከስ አባላት በባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ ለተፈናቀሉ ወገኖች አምስት ሚሊዮን 900ሺህ ብር የሚገመት ድጋፍ አደረጉ።
የኮከሱ አደረጃጀት ሰብሳቢ ወይዘሮ አበባዬ ገዛኽኝ በድጋፍ ርክክቡ ሥነ ሥርዓት ወቅት እንደገለጹት የአካባቢው ማኅበረሰብና በየደረጃው የሚገኘው የመንግሥት አካላት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም እያደረጉ ያሉት ጥረት የሚደነቅ ነው።
የኮከሱ አባላት ከተለያዩ የመንግሥትና ልማት ድርጅቶች ያገኙትን የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ፣ ምግብና አልባሳትን በማሰባሰብ ለተፈናቃዮቹ ማድረሳቸውን አስታውቀዋል።
ወይዘሮ አበባዬ እንዳሉት በወረዳው ከቀያቸው ተፈናቅለው ለነበሩ አባወራዎች ቤታቸው በአዲስ መልክ ተሰርቶላቸው ወደ ቀያቸው በመመለስ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ተፈናቅለው ከነበሩት ጋር በቀጥታ በመገናኘት ለማወቅ ችለዋል።
ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እስኪመለሱ ድረስ የተጀመረው ሰብዓዊ ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሚያደርጉት ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያጤኑትም ጠቁሟል።
የባሌ ዞን የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብረሃም ኃይሌ በበኩላቸው በተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ኮከስ አባላት ለተፈናቃዮቹ ለተደረገው ድጋፍ በዞኑ ሥም አመስግነዋል።
በወረዳው ተፈናቃዮችን በቋሚነት ለማቋቋም ከዞን እስከ ወረዳ ድረስ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ተፈናቃዮቹ ምግብና ምግብ ነክ ድጋፎች በተለያዩ አካላት እየተደረገላቸው መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው በተለይም የክረምት ወቅት እንዳያልፋቸው ለዘር የሚሆን ምርጥ ዘር በነፃ የተሰጣቸው መሆኑን አመልክተዋል።
የአፈር ማዳበሪያ በብድር መልክ እንዲያገኙ ሁኔታዎች እንደተመቻቸላቸውም ጠቅሰዋል።
ከተፈናቃዮቹ መካከል አቶ መንግሥቱ ገብረሥላሴ በሰጡት አስተያየት በተለያዩ አካላት የተደረገላቸው ድጋፍና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ በመደረጋቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል።
"የሰው ሕይወት እንዲጠፋ ምክንያት የሆኑና ንብረታችንን ያወደሙብን ጥቂት ፀረ ሰላም ኃይሎች ናቸው" ያሉት አቶ መንግሥቱ፤ ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በወንድማማችነት አብረው ለመኖር ወስነው ወደ ቀያቸው መመላሳቸውንም አመልክተዋል።
በአካባቢው በፀረ ሰላም ኃይሎች በተፈጸመው ድርጊት ማዘናቸውን የገለጹት ደግሞ ተፈናቃይ ወይዘሮ ማሽላ አድማሱ ናቸው።
መንግሥት እንዲህ ዓይነት እኩይ ተግባር በፈጸሙ አካላት ላይ እርምጃ በመውሰድ ጠንካራ አቋም መያዝ አለበት ብለዋል።
የአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ተወካይ ሼህ ሐሰን መሐመድ በበኩላቸው ከሰሞኑ በቀበሌያቸው በተሰራው አሳፋሪ ድርጊት ማዘናቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የአካባቢው ሰላም ወዳዱ ማኅበረሰብ የተፈጸመውን ተግባር ከመኮነን ባሻገር የተቃጠሉ ቤቶችን መልሶ በመገንባት ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ከፍተኛ ጥረት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ህልፈት ተከትሎ ሀዘናቸውን ለመግለጽ በወጡ ሰዎች ሽፋን በማድረግ ሁከት በፈጠሩ አካላት ምክንያት የሰው ሕይወት መጥፋቱና ከ1 ሺህ 400 የሚበልጡ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸው በወቅቱ ተገልጿል።