በሊባኖስ የሚኖሩ 234 ኢትዮጵያዊያን የመውጫ ቪዛ አገኙ - ኢዜአ አማርኛ
በሊባኖስ የሚኖሩ 234 ኢትዮጵያዊያን የመውጫ ቪዛ አገኙ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 19/2012 (ኢዜአ) በሊባኖስ የሚኖሩ 234 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው መመለስ የሚያስችላቸውን የመውጫ ቪዛ ማግኘታቸው ተገለጸ።
በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ቆንሱል ጄኔራል ተመስገን ኡመር የሊባኖስ የኢሚግሬሽን ጉዳዮች መስሪያ ቤት የጉዞ ሰነዳቸው ከተጠናቀቀላቸው ዜጎች መካከል ለ234ቱ የመውጫ ቪዛ መስጠቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።
የመውጫ ቪዛውን ያገኙት በስምንተኛው ዙር በሊባኖስ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው ሲሰሩ የቆዩና ቆንስላ ፅህፈት ቤቱ መረጃቸውን ለሊባኖስ የኢሚግሬሽንና ደህንነት ጉዳዮች መስሪያ ቤት የላከላቸው ዜጎች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ስምንተኛው ዙር በቀደሙት ሰባት ዙሮች የጉዞ ሰነዳቸው ተጠናቆ የመውጫ ቪዛ እንዲሰራላቸው ጥያቄ ቀርቦ ተቀባይነት ሳያገኝ የቀሩና ቆንስላ ፅህፈት ቤቱ መረጃቸውን እንደገና አሰባስቦ ለሊባኖስ ኢሚግሬሽንና ደህንነት ጉዳዮች መስሪያ ቤት የተላከበት እንደሆነም አመልክተዋል።
የጉዞ ሰነዳቸው ተጠናቆ የመውጫ ቪዛ እንዲሰራላቸው ወደ ሊባኖስ ኢሚግሬሽን ጉዳዮች መስሪያ ቤት የተላከላቸው ኢትዮጵያዊያንም ሂደቱ እንዳለቀ ቪዛ እንደሚመጣላቸው አቶ ተመስገን አስረድተዋል።
ቆንስላ ፅህፈት ቤቱ ስለ ጉዳዩ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝም አክለዋል።
ወደ አገራቸው ሲመለሱ የኮሮናቫይረስ ምርመራና ተያያዥ ጉዳዮችን ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ በጥቂት ቀናት ውስጥ በዝርዝር እንደሚያሳውቅም ጠቁመዋል።
የመውጫ ቪዛ የተሰራላቸው ዜጎች የትራንስፖርት ወጪያቸውን በራሳቸው እንደሚሸፍኑም አክለዋል።
ቪዛ የተሰራላቸው ዜጎች በእስር ቤቶች፣ በዲፓርቴሽን ማዕከል እንዲሁም በአሰሪዎቻቸው በደል ደርሶባቸው ድጋፍ ሲደረግላቸው የነበሩ ዜጎችን እንደማያካትት ገልጸዋል።
የሊባኖስ የኢሚግሬሽን ጉዳዮች መስሪያ ቤት ከዚህ ቀደም 450 ኢትዮጵያዊያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ ፈቃድ ሰጥቶ እንደነበር አውስተዋል።
ይሁንና በማጣራት ሂደት የስም ድግግሞሽና መስተካከል ያለባቸው ግድፈቶች በመገኘታቸው ወደ ኢትዮጵያ የመመለስ ፈቃድ ያገኙት ዜጎች ቁጥር 405 እንደሆነ ጠቅሰዋል።
በዘጠነኛው ዙር ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ 3 ሺህ 300 ዜጎች መመዝገባቸውንና መረጃቸው ለሊባኖስ ኢሚግሬሽን ጉዳይ መስሪያ ቤት መላኩንም ገልጸዋል።
የስምንተኛ ዙር እንደተጠናቀቀ ወደ ቀጣዩ ዙር ስራ እንደሚገባም ነው ያብራሩት።
በሊባኖስ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና በጎ ፈቃደኞች በወደብ ፍንዳታው በመጠለያ ለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙም አቶ ተመስገን ተናግረዋል።
በሊባኖስ ሕዝባዊ ተቃውሞ ከተነሳበት ከጥቅምት 2012 ዓ.ም ጀምሮ በሰባት ዙሮች 2 ሺህ 300 ኢትዮጵያዊያን ወደ አገራቸው መመለሳቸውን በቤይሩት ከኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
በአሁኑ ወቅት በሊባኖስ ከ400 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን እንደሚገኙ ይገመታል።