ሀገሪቱ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ እንዲሳካ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የደብረብርህ ከተማ ወጣቶች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገሪቱ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ እንዲሳካ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የደብረብርህ ከተማ ወጣቶች ገለጹ
ደብረ ብርሃን ነሐሴ 18/2012 (ኢዜአ) የሃገሪቱ የለውጥ ጉዞ እንዲሳካ የቀደሙ አባቶችን መከባበር፣ መቻቸል እና አብሮነት እሴት በመጠበቅ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የደብረብርህ ከተማ ወጣቶች ገለጹ።
ከወጣቶቹ መካከል አየለ ተረፈ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት፤ የሃገሪቱ የለውጥ ጉዞ የተሳካ እንዲሆን የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ የበኩሉን እንደሚወጣ ተናግሯል።
ለዘመናት በህዝቦች መካከል የቆየውን የአንድነት፣ የአብሮነትና የመተጋገዝ መልካም እሴት ለወጠበቅም እንዲሁ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢ የሚስተዋለው ከኢትዮጵያዊነት ባህል ያፈነገጠ ድርጊት ሊቀጥል እንደማይገባም ተናግሯል።
በተለይም የመቻቻል እሴቶችን በመሸርሸር ግጭትና ሁከት በማነሳሳት የህዝብ ደህንነትን ስጋት ላይ የሚጥሉ ኃይሎችን አጥብቀን እንታገላለን ብሏል።
''ከጥንት አባቶቻችን የተማርነው ሰላም፣ አንድነት፣ፍቅርና ወዳጅነት እንጂ ጥላቻና ግለኝነትን አልወረስነም'' ሲልም ገልጿል።
አሁን ላይ በሃገሪቱ የተጀመሩ ተስፋ ሰጭ የልማት ስራዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።
ወጣት መሰረት ደሳለኝ በበኩሏ በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ለዘመናት የተገነባው የህዝቦች አንድነት እንዳይሸረሸር በማስተዋል መንቀሳቀስ ይገባል ብላለች።
የኢትዮጰያ ህዝቦች በክፉም ደጉም ጊዜ በጋራ ተባብረው አሳልፈው ለዚህ ትውልድ ያደረሱ ቢሆንም የአባቶቻችን አደራ እየተወጣን አይደለም ብላለች።
ጠንካራ አንድነትና የበለፀገች ኢትዮጰያ እንድትገነባ በለውጥ ኃይል እየተሰሩ ያሉ የልማት ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ በአካባቢዋ የበኩሏን እንደምትወጣ ገልፃለች።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ደስታ አንዳርጌ እዳሉት የቀደሙ አባቶች ለሰላም፣ እኩልነትና ነፃነት የከፈሉትን ዋጋ ወጣቱ አክብሮ ሊጠብቅ ይገባል።
የአባቶችን የመስዋትነት ዋጋ በመስጠትም ሃገርን ወደ ብልጽግና ለማሻገር በሚደረገው ያልተቆጠበ ጥረት የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ወጣቱ የአካባቢውን ብሎም የሀገሪቱን ሰላም በማስጠበቅ ግንባር ቀደም ሊሆን ይገባል ያሉት አቶ ደስታ
መንግስትም ለወጣቶች በስራ እድል ፈጠራ እንዲጠቀም በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ዜጎች በሃገራቸው ያለገደብ ተዘዋውረው የመስራትና የመኖር መብት እንዲከበር ጠንካራ አንድነት ፈጥሮ መሥራት ይገባል ያሉት ደግሞ በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃድቅ ናቸው።
አባቶች ያቆየቱን አንድነት እና በሰላም አብሮ የመኖር ጥበብ ለማሰቀጠል ወጣቱ ትውልድ የጀመረውን አካባቢን የመጠበቅና የማልማት ሥራ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል
የዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ መታሰቢያ የአረጓዴ ልማት ፓርክ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ሰሞኑን በደብረ ብርሃን ከተማ መቀመጡን ኢዜአ በወቅቱ ዘግቧል።