የአባይ ወንዝ ትርክትን በሚገባ ማስተዋወቅና ማስረዳት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የአባይ ወንዝ ትርክትን በሚገባ ማስተዋወቅና ማስረዳት ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 17/2012(ኢዜአ) የአባይ ወንዝ ትርክትን በሚገባ ማስተዋወቅና ማስረዳት እንደሚገባ ተገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር "አባይ ለኢትዮጵያ ህይወትና ኩራት ነው" በሚል መሪ ቃል በዙም መተግበሪያ ያዘጋጀው የበይነ መረብ የውይይት መድረክ (ዌቢናር) ዛሬ ተካሄዷል።
በአባይ ወንዝና በኢትዮጵያ ውሃ ሃብቶች ጥናትና ምርምር ያደረጉ ባለሙያዎች በውይይት መድረኩ ላይ የመነሻ ጽሆፎች አቅርበዋል።
አባይ: የሕግ ማዕቀፍ ተግዳሮቶች፣ አባይ: የኢትዮጵያ ህይወት ስነ ውሃ ኢኮኖሚ ፋይዳና አገራዊ እድገት፣ አባይ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ፣ አባይ: ለኢትዮጵያ ማንነት ኩራትና ክብር እና አባይና አገራዊ ግንባታ: የአባይ ውጫዊ ፈተናዎችና አባይ በሚሉ ርዕሶች ጽሁፎቹ ቀርበዋል።
የውሃ ሃብቶች ተመራማሪ ወይዘሪት መቅደላዊት መሳይ የአባይ ወንዝ ከ90 እስከ 95 በመቶ የኢትዮጵያ ህዝብ ህይወቱ የተመሰረተበት በመሆኑ አባይን መጠቀም ምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጻለች።
አባይ የህልውናችን ጉዳይ ነው ስንል ለማለት ብቻ ሳይሆን ከመብላትና ከመጠጣት፣ ከመኖር አለመኖር፣ ከማደግና ካለማደግ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ነው በማለት ተናግራለች።
በተለያዩ ገጾች የአባይ ወንዝ ያሉት ቱሩፋቶች በርካታ በመሆናቸው ወንዙን ሌሎች የውሃ ሀብቶችን በመጠቀም የኢትዮጵያን እድገትና ልማት ማረጋጥ ይገባል ብላለች።
የህግ ማዕቀፎችን አስመልክቶ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ መሐመድ እሸቱ ኢትዮጵያ አሁን በምታደርገው የሶስትዮሽ ድርድር የውሃ ክፍፍል ጉዳይ ሊነሳ አይገባውም ብለዋል።
እ.አ.አ በ2015 በሱዳን መዲና ካርቱም የተፈረመውን የመርሆዎች መግለጫ ስምምነት እንደ መስፈንጠሪያ ተጠቅሞ ግብጽና ሱዳንን የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት መድረክ እንደሚመጡ ማድረግ የሚያስችል ስራ መስራት እንደሚገባም ገልጸዋል።
የህዳሴ ግድብ ወደ ትብብር ማዕቀፉ አገራቱን ለማምጣት ትልቅ አጋጣሚ እንደሆነና ይሄም ፍትሐዊ የሆነ ስምምነት ለማድረግ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
በድርድሩ የሚነሱ ሀሳቦችና አጀንዳዎች ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አክለዋል።
የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው የአባይ ወንዝ ከክርስቶስ ልደት በፊት እስከ አሁን ባለው ሁኔታ መልካምና ጥሩ የማይባሉ የታሪክ ክስተቶች ያስተናገደ ነው ብለዋል።
ወደ መጀመሪያው አካባቢ ከግብጽ ጋር የጥሩ ግንኙነት መመስረቻ እንደነበረና በጊዜ ሂደት ግን ኢትዮጵያ አባይ ወንዝን እንዳትተጠቀም በግብጽና በአውሮፓ አገራት ተጽእኖ እንደደረሰባት አውስተዋል።
እ.አ.አ ከ2003 የአባይ ወንዝ ኢትዮጵያ ለመጠቀም የያዘችው አቋም መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን አመልክተዋል።
የአባይ ወንዝ ለመጠቀም የጋራ አንድነትና ህብረት እንደሚያስፈልግ ይሄም በአገር ውስጥና በውጭ የሚፈጠረውን ጫና መቋቋም እንደሚያስችልና ታሪክም ይሄን እንደሚያስተምር ገልጸዋል።
የአባይ ወንዝ ጉልበቱ ገባሮቹ እንደሆኑና ከአባይ ውጪም ሌሎች ገባር ወንዞችንም በመጠቀም ኢትዮጵያን ማሳደግ እንደሚቻል ጠቅሰዋል።
የፍልስፍና ተመራማሪ ዶክተር ግርማ መሐመድ የአባይ ወንዝ በኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ እልህ፣ ግብግብ፣ ድርድር፣ እርቅ፣ ኩራትና ሰላምን መፍጠር የሚባሉ እሴቶችና ማንነቶች መፍጠሩን ገልጸዋል።
አባይ ወደ ታች መፍሰሱን መቀጠሉ ተፈጥሯዊ ሂደት መሆኑን መቀበል እንደሚያስፈልግና ይሄን አለመቀበል ግን ወንድሞቻችንን ይጎዳል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ያላቸውን አቅም አባይ ውስጥ ካለው አቅም ጋር በማስተባበር አባይ ወንዝን አልምቶ ብሔራዊ ኩራት ማድረግ እንደሚቻልም ተናግረዋል።
የምስራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ የአባይ ወንዝና የህዳሴ ግድብ እንዲሁም የውሃ ሀብቶችን የመጠቀም ፍላጎት የጋራ መግባባትና አቋም በመያዝ አገር ለመገንባት እንደ መነሻ ሀሳብ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውስጣዊ ልዩነቶችን ለመፍታትና ውጫዊ ተጽእኖን ለመቋቋም ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
አገራዊ ግንባታና አገረ መንግስት ግንባታ ላይ ያሉ የታሪክ፣ የተቋማትና የአመራር ተግዳሮቶች በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ ገልጸው፤ አገራዊ ፕሮጀክቶች ከዚህ አንጻር የሚፈጥሩት እድል ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአባይ ወንዝ በኢትዮጵያ ታሪክ የተወደሰ የተወቀሰ በመጽሐፍትና በጥናታዊ ጽሁፎች ብዙ የተባለለት የውሃ ሀብት ነው ብለዋል።
በአሁኑ ሰአት የአባይ ወንዝ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጠቀም ጅማሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ትልቅ መነቃቃትና ተስፋን የጫረ መሆኑን ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከሃይል ማመንጨት ባለፈ በአሳ ሀብት ልማትና በቱሪዝም የሚያስገኘው ፋይዳ የጎላ እንደሆነና "አባይን ለመጠቀም ጉዞ ጀምረናል" ብለዋል።
የአባይ ወንዝ ትርክት ወንዙ ለኢትዮጵያ ህይወትና ኩራት በመሆኑ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በሚገባ ማስተዋወቅና ማስረዳት እንደሚገባ አመልክተዋል።
የአባይ ወንዝ ልዕልና፣ የአባይ ወንዝ ትልቅነት፣ የአባይ ወንዝ የኢትዮጵያ ከፍታ፣ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የነጻነት ተምሳሌት ብሔራዊ አርማ መሆኑን አጉልቶ ማሳየት ነው ሲሉም አቶ ገዱ ያስረዱት።
በአባይ ወንዝ የራሳችን የሆነ አገላለጽ መፍጠር እንደሚያስፈልግና አባይ የመግባቢያና የመለያነታችን መገለጫ እንዲሆን መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ለዚህም ወጣቶች ባላቸው ጉልበትና እውቀት የበኩላቸውን ሃላፊነት መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የአባይ ወንዝን በስርዓተ ትምህርት ውስጥ ማካተት እንደሚያስፈግና ይሄም በጥናትና እውቀት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ምሁራን ያላቸው ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ህግ ሆኖ ወደ ስራ እንዲገባ በተፋሰሱ አገራት ፓርላማ ማጽደቅ እንደሚገባና በዚህ ላይም መንግስት ጥረት እያደረገ መሆኑን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያብራሩት።
በቀረቡት ጽሁፎች ላይ ከውይይቱ ተሳታፊዎች አስተያየቶችና ጥያቄዎች ተነስተው ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
የዛሬው ውይይት በተከታታይ ወጣቶችን፣ ሴቶች፣ ምሁራንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በማካተት እንደሚቀጥል በበይነ መረብ መድረኩ (ዌቢናሩ) ተገልጿል።